በሳምንቱ የመክፈቻ ቀን ጨዋታ በውድድር ዓመቱ የሊጉን ባለክብር ይወስናል? ወይስ ቻምፒዮኑን ለመለየት ሌሎች የጨዋታ ሳምንታትን ያስጠብቃል? ፤ የመጀመሪያው የሊጉ ወራጅ ዛሬ ይታወቃል? ወይስ? የሚለውን ለማወቅ የሚደረጉ ተጠባቂ ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ኢትዮጵያ ቡና
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ በ45 ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዞ የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ወደ ውድድሩ ማጠናቀቂያ እየተጠጋ በሄደ ቁጥር ተለዋዋጭ የውጤት ጉዞ እያስመለከተን ይገኛል። ቡድኑ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች 1 ድል፣ 2 አቻ እና 2 ሽንፈት ያስመዘገበ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንት በአዳማ ከተማ 2 ለ 1 መሸነፉ የቀደመውን መረጋጋት እንዳጣ የሚያመላክት ነው። በ35 ጨዋታዎች 43 ጎል አስቆጥሮ 41 ጎሎችን ያስተናገደው ንግድ ባንክ የ+2 የጎል ክፍያ ያለው ቢሆንም በተከላካይ ክፍሉ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ዋጋ እያስከፈሉት ይገኛሉ። ዛሬ ከወራጅ ቀጠናው የነጥብ ስጋት ሙሉ በሙሉ ለመራቅና ደህንነቱን ለማረጋገጥ የሚጫወተው ባንክ ከፍ ያለ የማጥቃት አቅሙን ተጠቅሞ በመሃል ሜዳ ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ የባላጋራውን የተከላካይ መስመር ለመስበር ታክቲካዊ አቀራረብ ይዞ እንደሚገባ ይጠበቃል።
በአንጻሩ በ46 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የአሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ስብስብ ኢትዮጵያ ቡና ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች እንደ ተጋጣሚው ሁሉ 1 ድል፣ 1 አቻ እና 3 ሽንፈት በማስተናገድ በተለይ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ተከታታይ ሽንፈት ገጥሞታል። በ35 ጨዋታዎች 37 ጎሎችን አስቆጥሮ 39 ጎሎችን ያስተናገደውና የ-2 የጎል ዕዳ ያለበት ቡና በኋለኛው ክፍል ላይ የሚታይበትን የመዘናጋት ችግር ካልቀረፈ ዛሬም በጠንካራ የንግድ ባንክ አጥቂዎች ከባድ ፈተና ሊገጥመው ይችላል። ቡድኑ አሁን ካለበት መካከለኛ ደረጃ ከፍ ለማለትና የክለቡን ስም የሚመጥን የደረጃ ማሻሻያ ለማድረግ የዛሬውን ጨዋታ በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ይኖርበታል። ለዚህም የንግድ ባንክን የኋላ ክፍል ድክመት ለማጥቃት ፈጣን የመሃል ሜዳ ሽግግሩን እና የተጫዋቾችን የኳስ ቅብብል ፍሰት ታክቲክ እንደ ዋና የጨዋታ ስትራቴጂ መጠቀም ከቻሉ የሶስት ነጥብ ባለቤት የመሆናቸው ዕድል ከፍ ያለ ነው።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዛሬው ጨዋታ ሳይመን ፒተር፣ ቢንያም ካሳሁን እና ኤፍሬም ሌጋሞ በቅጣት ምክንያት የሚያጣ ሲሆን አዲስ ግዳይም በዚህ ጨዋታ የመኖሩ ነገር አጠራጣሪ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 39 ጊዜ ተገናኝተው ቡና 19 ጨዋታ በማሸነፍ የበላይነት ይዟል። ባንክ 10 ሲያሸንፍ በቀሪው 10 ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። ቡና 59 ጎሎች ፣ ባንክ 42 ጎሎችን ማስቆጠርም ችለዋል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ሸገር ከተማ
በ35 ነጥብ እና በ-17 የጎል ክፍያ በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ 20ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ከፍተኛ የመውረድ አደጋ ያንዣበበበት ድሬዳዋ ከተማ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች 1 አቻ እና 4 ሽንፈት በማስተናገድ አዙሪት የውጤት ቀውስ ውስጥ ይገኛል። በ35 ጨዋታዎች 22 ጎል ብቻ አስቆጥሮ 39 ያስተናገደው ድሬዳዋ በሊጉ እጅግ ደካማው የማጥቃት መስመር ያለው ስብስብ በመሆኑ ባለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻሉ ሲሆን ከዘጠኙም ጨዋታ አራት ግቦችን ብቻ ማስመዝገባቸው ብድኑ ያለበትን እጅግ አስከፊ ሁኔታ የሚያሳይ ነው። በሊጉ የመቆየት ተስፋውን በተአምር ለማለምለምና ከደረጃ ሰንጠረዡ የመጨረሻ ስፍራ ፈልቅቆ ለመውጣት የዛሬው ጨዋታ ለድሬዳዋ ከተማ ፍጹም የሞት ሽረት ፍልሚያ ነው፤ በመሆኑም ቡድኑ ካለበት ከፍተኛ የስነ ልቦና ጫና ወጥቶ የተከላካይ ክፍሉን በማጠናከርና የሚፈጠሩ ጥቂት አጋጣሚዎችን ወደ ጎል በመቀየር ነጥብ ለመያዝ ይገደዳል።
በሌላ በኩል በ44 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሸገር ከተማ ምንም እንኳን በአንጻራዊነት የተሻለ አቀማመጥ ላይ ቢመስልም አራት ቡድኖች በሚወርዱበት በዚህ የውድድር ዓመት ቀሪ ጨዋታዎች እያሉ ገና ሙሉ በሙሉ ከወራጅነት ስጋት ነፃ አልሆነም። ቡድኑ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች 2 ድል፣ 2 ሽንፈት እና 1 አቻ ያስመዘገበ ሲሆን በቅርብ ጨዋታው ከወልዋሎ ጋር ያለ ጎል አቻ መለያየቱ ይታወሳል። በ35 ጨዋታዎች 30 ጎል አስቆጥሮ 29 ያስተናገደውና የ+1 የግብ ክፍያ ያለው ስብስብ ከድሬዳዋ በተሻለ የተመጣጠነ የማጥቃትና የመከላከል መዋቅር ቢኖረውም የዛሬው ጨዋታ ለእነሱም ቢሆን ቀሪ ሳምንታትን በሰላም ለመጨረስና ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን ለማዳን የሚደረግ ወሳኝ የታክቲክ ፍልሚያ ነው።
ድሬዳዋ ከተማ መሐመድኑር ናስር፣ አስቻለው ታመነ፣ አህመድ ረሺድና ዘራይ ገ/ሥላሴን በህመም ምክንያት ዛሬ አያገኝም። በሸገር ከተማ በኩል ሁሉም የቡድኑ አባላቶች ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው::
ሁለቱ ቡድኖች ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ጨዋታቸውም ያለግብ ዜሮ ለዜሮ በሆነ ውጤት ተጠናቋል::
ሲዳማ ቡና ከ ነጌሌ አርሲ
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በአሁኑ ወቅት በ64 ነጥብ እና በ+20 አስደናቂ የጎል ክፍያ የደረጃ ሰንጠረዡን አናት ለረጅም ሳምንታት በፅኑ ተቆጣጥሮ ይገኛል:: ቡድኑ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በሶስቱ ተከታታይ ድሎችን ጨምሮ 3 ድል እና 2 ሽንፈት ያስመዘገበ ሲሆን በቅርብ በዚህም የበፊቱን ግርማ ሞገስ መልሶ አግኝቷል። በ35 ጨዋታዎች 41 ጎል አስቆጥሮ 21 ጎል ብቻ ያስተናገደው ሲዳማ ቡና በሊጉ ጠንካራውና በቀላሉ የማይበገረው የተከላካይ መስመር ባለቤት ነው። ዛሬ የሚደረገው ፍልሚያ ለሲዳማ ቡና በውድድር ዓመቱ እጅግ ታላቅና ተጠባቂ ምዕራፍ ነው፤ ምክንያቱም ክለቡ በዛሬው ጨዋታ ነጥብ መጋራት ወይም ድል ማድረግ የሚችል ከሆነ የ2018 የሲቢኤ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን መሆኑን በይፋ የሚያውጅበት ታሪካዊ አጋጣሚ ይሆንለታል። በመሆኑም ቡድኑ የተለመደውን የታክቲክ ዲሲፕሊን በመጠበቅ እና የመሃል ሜዳ ቁጥጥርን በማጥበቅ ዋንጫውን ዛሬውኑ በእጁ ለማስገባት ወደ ሜዳ ይገባል።
በሌላ በኩል በ56 ነጥብ የደረጃ ሰንጠረዡን 2ኛ ደረጃ በመያዝ የሊጉ የቅርብ ተፎካካሪ የሆነው ነጌሌ አርሲ ካለፉት አምስት ጨዋታዎች 2 ድል፣ 2 አቻ እና 1 ሽንፈት ያስመዘገበ ሲሆን በቅርብ ጨዋታው ሀዋሳ ከተማን 2 ለ 1 ማሸነፉ ለዛሬው ታላቅ ፍልሚያ ትልቅ ስነ ልቦናዊ ስንቅ ይሆነዋል። በ35 ጨዋታዎች 34 ጎል አስቆጥሮ 26 ያስተናገደውና የ+8 የጎል ክፍያ ያለው ነጌሌ አርሲ፣ በሊጉ ውጤታማና ሚዛናዊ የጨዋታ ስልት ካላቸው ክለቦች አንዱ ነው። ነጌሌ አርሲዎች በዋንጫው ፉክክር ውስጥ እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ ጸንተው ለመቆየት ዛሬ የሲዳማ ቡናን የአሸናፊነት ጉዞ መግታት እና በመካከላቸው ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ ግዴታቸው እንደሆነ ያውቃሉ። ይህ የሁለቱ ክለቦች ከፍተኛ ፍላጎት ጨዋታውን እጅግ ብርቱ ፉክክር የሚታይበትና በስፖርት አፍቃሪያኑ ዘንድ በጉጉት የሚጠበቅ ያደርገዋል።
በሲዳማ በኩል ጉዳት ላይ የሰነበተው አቤል ያለው ወደ ልምምድ ቢመለስም ለዛሬው ጨዋታ የመድረሱ ነገር ግን አጠራጣሪ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ያንን ጨዋታ ነገሌ አርሲ አንድ ለዜሮ በሆነ ውጤት ድል አድርጓል።

