ሪፖርት | የጦና ንቦች ወደ ድል ሲመለሱ ኤሌክትሪክ እና መቐለ አቻ ተለያይተዋል

ሪፖርት | የጦና ንቦች ወደ ድል ሲመለሱ ኤሌክትሪክ እና መቐለ አቻ ተለያይተዋል

በጨዋታ ሳምንቱ በመጨረሻ ቀን በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ወላይታ ድቻ ባህርዳር ከተማን 2ለ0 ሲያሸንፍ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ምዓም አናብስት ነጥብ ተጋርተዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ መቐለ 70 እንደርታ

ከዝናብ ጋር ታጅቦ ጅማሮውን ያደረገው ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከመቐለ 70 እንደርታ ያገናኘው የእለቱ ቀዳሚው ጨዋታ ምዓም አናብስት ከውጤቱ አስፈላጊነት አንፃር ጫን ብለው እየገቡ ግብ ለማስቆጠር የጣሩበትን የመጀመሪያ አጋማሽ የተመለከትን ሲሆን በተለይም ብርሃኑ አዳሙ ሳጥን ውስጥ ተከላካዮችን ቀንሶ ያለቀ ኳስ ሲያሻግር ቦና ዓሊ ግብ ጠባቂውም ሳይኖር ብቻውን ሆኖ አግኝቶ መረጋጋት ተስኖት ያመከነው አስቆጪው አጋጣሚ እንዲሁም ከሳጥን ውጭ ሆኖ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው እንዴትም ጨርፎ ያወጣባቸው ሙከራዎች ቀዳሚ ሊያደርጋቸው የቀረቡ ነበሩ።

ከተጋጣሚያቸው ጋር ተመጣጣኝ የኳስ ቁጥጥር ቢያደርጉም ወደፊት በመሄድ ረገድ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ያተኮሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች የጨዋታ ጅማሮ ላይ ኢዮብ ገብረማርያም በመሰመር በኩል ኳስ በፍጥነት ይዞ ገብቶ አድርጎት ሶፎንያስ ያገደበት ሙከራ ሲጠቀስ አጋማሹም ግብ ሳይቆጠርበት ተገባዶ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከመልበሻ ክፍል መልስ ጨዋታው ጠንከር ባለ ፉክክር ሲመለስ ምዓም አናብስት በሙሉ ኃይላቸው ወደ ተጋጣሚ ግብ ክልል እየደረሱ አደገኛ እና አስቆጪ አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል። ብርሃኑ አዳሙ ግብ ጠባቂውን አልፎ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ሲመታት ያሬድ የማነ ከየት መጣ ሳይባል ተንሸራቶ የተከላከለበት አስቆጪው አጋጣሚ እና ቦና አሊ በመስመር በኩል ኳስ ይዞ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ያሻገረለትን ኳስ አብዱለጢፍ ባምባ ጠንከር ያለ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው ዮሱፉ ሞሩ በግሩም ሁኔታ ያዳነባቸው ሙከራዎች ሶስት ነጥብ ሊያስገኝላቸው የተቃረቡ ተጠቃሽ አጋጣሚዎች ነበሩ።

ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ በመልሶ ማጥቃት ሲገቡ የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች እንዲሁ ግብ ለማግኘት ጥረት ያደረጉ ቢሆንም የጨዋታ ብልጫ በነበራቸው ምዓም አናብስት ግብ የሚያስተናግዱ እየመሰለ ጨዋታው ቢቀጥልም ግብ ሳያስመለክተን ነጥብ በማጋራት ተቋጭቷል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

በጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ ቀን በአዲስ አበባ ስታዲየም ባህርዳር ከተማን ከወላይታ ድቻ ያገናኘው ሁለተኛው ጨዋታ በተመጣጣኝ የጨዋታ እንቅስቃሴ ጅማሮውን ሲያደርግ ቡድኖቹ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ዘለግ ያለ ደቂቃዎች ሲቆጠሩ ወላይታ ድቻዎች በመጀመሪያ አደገኛ ሙከራ መሪ የሆኑበትን ግብ አስቆጥረዋል። ጨዋታው 33ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ቴዎድሮስ ታፈሰ ከተከላካይ ጀርባ የጣለውን ኳስ ያሬድ ዳርዛ በፍጥነት ሾልኮ በመውጣት በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ የጦና ንቦችን ቀዳሚ አድርጓቸዋል።

አንፃራዊ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው የጣና ሞገዶች ወደፊት ሄደው ምላሽ ለመስጠት ሲጥሩ የተመለከትን ቢሆንም በአጋማሹ ወደ ፊት ሄደው የሚያደርጉት ሙከራ የተጋጣሚያቸውን የግብ ዘብ መፈተን ሳይችል እየቀረ እያስተዋልን የመጀመሪያ አጋማሽ እየተመሩ ወደ መልበሻ ክፍል እንዲገቡ ሆኗል።

ጨዋታው እንደተመለሰ ጠንከር ብለው የተመለሱት የጦና ንቦች መሪነታቸው ያሰፉበትን ግብ አስቆጥረዋል። 48ኛው ደቂቃ ላይ ከራሳቸው ሜዳ በረጅሙ የተሻገረውን ኳስ ያሬድ ዳርዛ በፍጥነት ደርሶ ግብ ጠባቂው መውጣቱን አይቶ በግብ ጠባቂው አናት በግሩም ሁኔታ በማሻገር ግሩም ግብ ከርቀት ማስቆጠር ችሏል።

የጣና ሞገዶች ወደ ጨዋታ ለመመለስ በቁጥር በዛ ብለው እየገቡ የጦና ንቦችን ተከላካይ መስመር እንዲሁም ግብ ጠባቂያቸውን ሲፈትኑ እያስተዋልን አስቆጪ እና አደገኛ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ያስተዋልን ቢሆንም የያዙትን ነጥብ አስጠብቀው ለመውጣት ወደኋላ አፈግፍገው መከላከሉ ላይ ትኩረትን ያደረጉት የወላይታ ድቻ ተከላካይ መስመር አልፈው ኳስን መረብ ማገናኘት ተስኗቸው ጨዋታው 2ለ0 በሆነ ውጤት ለጦና ንቦች ሦስት ነጥብ በማስገኘት ተጠናቋል።