አርባምንጭ ከተማ በዐፄዎቹ 2ለ0 ተሸንፎ ከሊጉ መውረዱን ሲያረጋግጥ ሀዲያ ሆሳዕና ወልዋሎን በማሸነፍ ወሳኝ ድል ተቀዳጅቷል።

ፋሲል ከነማ ከ አርባምንጭ ከተማ
ፋሲል ከነማን ከአርባምንጭ ከተማ ያገናኘው በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በተደረገው ቀዳሚ ጨዋታ ዐፄዎቹ በተሻለ እንቅስቃሴ ጅማሮውን ማድረግ የቻሉ ሲሆን ከተደጋጋሚ ሙከራ በኋላም ግብ ማስቆጠር ችለዋል። 25ኛው ደቂቃ ላይ ዳግም አወቀ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ የአዞዎቹ ተከላካይ እና ግብ ጠባቂ መግባባት ተስኗቸው ኳሱ ተጨርፎ ሲሻገር ብቻውን ሆኖ ሲጠባብቅ የነበረው ታምራት ኢያሱ በቀላል ንክኪ ወደ ግብነት ቀይሮታል።

ሙከራዎችን በማድረግ አኳያ በቁጥር ደረጃ ብልጫ የነበራቸው አዞዎቹ ግብ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ሲሆን በተለየም ግብ ካስተናገዱ በኋላ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ወደፊት እየገቡ በጄሮም ፈሊፕ አማካኝነት ሳጥን ውስጥ ሆነው ያደረጉት ጠንከር ያለ ሙከራ ሲጠቀስ ግብ ጠባቂው ጨርፎ ባያወጣባቸው አቻ ሆነው መልበሻ ክፍል እንዲገቡ ሊያደርጋቸው የቀረበ አጋጣሚ ቢሆንም በአጋማሹ ግብ ሳያስቆጥሩ ተገባዶ ለእረፍት ለመውጣት ተገደዋል።
የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንዲሁም ግብ ለማግባት በሚደረግ እንቅስቃሴ የተሸሉ ሆነው የተመለሱት አዞዎቹ የሚያገኙት ኳስ በሙሉ ግብነት ለመቀየር ቶሎ ወደ ተጋጣሚያቸው ግብ ክልል እየጣሉ ተደጋጋሚ ጥረት ሲያደርጉ እያስተዋልን አሸናፊ ተገኝ ከጄሮም ፈሊፕ የተሻገረውን ኳስ አክርሮ መትቶ ያደረገውን ሙከራ ተጠቃሽ የነበረ ሲሆን ዐፄዎቹ የአርባምንጮችን ጫና እየተከላከሉ እንዲሁም በመልሶ ማጥቃት ረጃጅም ኳሶችን እያሻገሩ ቆይተው ተጨማሪ ግብ ማግኘት ችለዋል። 79ኛው ደቂቃ ላይ ከእራሳቸው ሜዳ በመልሶ ማጥቃት ኳስ ያገኘው ታምራት ኢያሱ በግል ጥረቱ መሬት ለመሬት ተከላካዮችን አታሎ በማለፍ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ በቀላሉ በማሻገር ከመረብ ጋር አገናኝቶ መሪነታቸውን አጠናክሯል።

በሊጉ ለመቆየት ግዴታ ማሸነፍ የሚጠበቅባቸው አዞዎቹ እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በሙሉ ኃይላቸው እያጠቁ ግብ ለማገኝት ጥረት ያደረጉ ቢሆንም የዐፄዎቹ ተከላካይ መስመር ጠንካራ በመሆኑ ግብ ለማስቆጠር ተቸግረው ሽንፈት በማስተናገድ ጨዋታው ተጠናቆ ለከርሞ በሊጉ ለመቆየት የሚያስችላቸው ውጤት በህሳባዊ ስለት ባለመኖሩ ከሊጉ የወረደ የመጀመሪያ ቡድን ሆነዋል።
ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ከ ሀዲያ ሆሳዕና
የጨዋታ ሳምንቱ ማሳረጊያ የሆነው ቢጫ ለባሾቹን ከነብሮቹ ያገናኘው ጨዋታ በፈጣን ሽግግሮች የታጀበ እንዲሁም ሁለቱም ቡድኖች ካሉበት ከወራጅ ቀጠና ስጋት ለመውጣት ቀዳሚ ለመሆን እረፍት የለሽ እንቅስቃሴ እያደረጉ ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል። አንፃራዊ ብልጫ የነበራቸው ቢጫ ለባሾቹ ከማዕዘን ተሻምቶ ተጨራርፎ የደረሰውን ኳስ ሙሉዓለም መስፍን በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ ጠንካራ ሙከራ ሲያደርግ የነብሮቹ ተከላካዮች እንዴትም ያገዱበት አደገኛው ሙከራ፣ ፍሬው ሰለሞን እና ያሬድ ከበደ ባደረጉት ጥሩ መግባባት ያሬድ ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ መትቶ ግብ ጠባቂው የተቆጣጠረበት ሌላኛው ሙከራ በአጋማሹ ተጠቃሽ ነበሩ።

በመልሶ ማጥቃት ቀዳሚ ለመሆን ሲጥሩ የነበሩት ነብሮቹ በአጋማሹ ግብ ለማግኘት እየጣሩ ቆይተው የአጋማሽ መጠናቀቂያ ላይ ግብ አግኝተዋል። ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሙታኩዋ ጆል በቀላሉ ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርግ ኳሱ አምልጦት ብሩክ በየነ በግሩም መጀመሪያ ንክኪ ኳሱን ተቆጣጥሮ ተቀልብሶ በመምታት ወደግብነት ቀይሮ እየመሩ መልበሻ ክፍል እንዲገቡ አስችሏቸዋል።

ጨዋታው ከእረፍት ሲመለስ ቢጫ ለባሾቹ ፍፁም የጨዋታ በላይነት ወስደው በፈጣን ሽግግር በቁጥር በዛ ብለው እያጠቁ አደገኛ ሙከራዎን እንዲሁም አስቆጪ የሚባለ አጋጣሚዎች የፈጠሩ ሲሆን ከእነዛ መካከል ሀፊዝ ኮንኮኒ እና ሰመረ ሀፍታይ አከታትለው ከሳጥን ውጪ ያደረጓቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት ወደኋላ አፈግፍገው በመጫወት መከላከሉ ላይ ሙሉ ትኩረት ያደረጉት ነብሮቹ አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለጊዜ የራሳቸው ሜዳ ክፍል ላይ አድርገዋል። ጨዋታውም በብሩክ በየነ ብቸኛ ግብ ለነብሮቹ ወሳኝ ሦስት ነጥብ በማስገኘት ጨዋታው ተጠናቋል።

