ወላይታ ዲቻዎች ከዘጠኝ ተከታታይ ያለመሸነፍ ጉዞ በኋላ በኢትዮ ኤሌክትሪክ ሸንፈትን በማስተናገድ እጃቸውን ሰጥተዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ የሁለቱ ቡድኖች ፉክክር ይበልጥ ተጠቃሽ የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ የጦና ንቦቹ በጥቂቱ የተሻለ ፍላጎት አሳይተውበት የነበረ ሲሆን በኬኔዲ አባተ እና በ መልካም ቦጋለ ካደረጓቸው ሙከራዎች በኋላ በተለይም በማጥቃት መስመር ላይ የፈጠሩት ጫና በመጨረሻም በ40ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬ አፍርቶ መሪ መሆን የሚያስችላቸውን ግብ አስመዝግበዋል። ከወገብ በላይ ከፍ ተደርጎ ወደ ሳጥን ውስጥ የተሻማውን ኳስ ብሩክ ኤልያስ ወደ ግብ የሞከረው ቢሆንም የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ግብ ጠባቂ የሱፍ ሞሮ ኳሷን በአግባቡ መቆጣጠር ተስኖት ከእጁ ስትመለስ በቅርብ ርቀት ላይ ይጠብቅ የነበረው ያሬድ ዳርዛ ያገኘውን አጋጣሚ ተጠቅሞ ኳሷን በቀላሉ መረቡ ላይ በማሳረፍ ወላይታ ዲቻን እ መሪ ማድረግ የሚቻለውን አስቆጥሯል።

ይሁን እንጂ የጦና ንቦቹ ይዘውት የነበረው መሪነትና የደስታ ድባብ መዝለቅ የቻለው ለአራት ደቂቃዎች ብቻ የነበረ ሲሆን የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩ 44ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተሻገረው ኳስ አቤል ሀብታሙ በጥሩ የአየር ላይ ፍልሚያ ኳሷን አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው የቀድሞ የወላይታ ዲቻ ተጫዋች የነበረው በረከት ወልደዮሐንስ በጥሩ አጨራረስ መረብ ላይ አሳርፏታል። ይህች ግብም ኤሌክትሪኮችን ገና ከእረፍት በፊት ወደ አቻነት የመለሰች ሲሆን የመጀመሪያው አጋማሽም በሁለቱ ቡድኖች 1ለ1 አጓጊ ውጤት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ የጦና ንቦቹ የተከላካይ መስመርን በሚሰነጥቁ ኳሶች ክፍተቶችን ለመፈለግ የጣሩ ሲሆን በ56ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ዳርዛ ከግብ ጠባቂ ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው ዕድል እጅግ አስቆጪ ነበር። በአንጻሩ ጥንቃቄ በተሞላበት ማጥቃት የተሻሉት ኤሌክትሪኮች ከአስር ደቂቃዎች በኋላ የጨዋታውን መልክ ቀይረውታል በ66ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ የማነ ከግራ መስመር ያሻማውን ስስ ኳስ አቤል ሀብታሙ በጥሩ የአየር ላይ አቋቋም በግንባሩ ገጭቶ መረብ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታውም በኢትዮ ኤሌክትሪክ 2ለ1 ባለድልነት የተጠናቀቀ ሲሆን ይህ ውጤትም ወላይታ ዲቻ ከዘጠኝ ተከታታይ ጨዋታዎች ያልተደፈረበትን ድንቅ ጉዞ ገትቶ የመጀመሪያ ሽንፈቱን እንዲያስተናግድ አስገድዶታል።ተ

