በአዳማ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ድሬዳዋ ከነብሮቹ አቻ ተለያይቶ ከሊጉ መውረዳቸው ሲያረጋግጡ ምድረገነት ሽረ መድንን 3ለ0 በማሸነፍ ወሳኝ ድል ተቀዳጅቷል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከ ድሬዳዋ ከተማ
ሀዲያ ሆሳዕና ከ ከድሬዳዋ ከተማ ያገናኘው ቀዳሚው ጨዋታ በተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ጥሩ ፉክክር ታይቶበታል። የተሻለ የግብ ማግባት ሙከራ በማድረግ ረገድ የተሻሉ የነበሩት ብርቱካናማዎቹ ሲሆኑ አቤል አሰበ አድርጎት ግብ ጠባቂው ያወጣባቸው እንዲሁም አብዲሳ ጀማል ከመስመር የተሻማውን ኳስ ጨርፎ ለጥቂት ከግቡ ቋሚ ብረት ርቆ ያለፈባቸው ሌላኛው ሙከራ ይጠቀሳል።

ወደፊት እየሄዱ የተጋጣሚያቸውን ተከላካይ መስመር ሲፈትኑ የነበሩት ነብሮቹ ኢዮብ ዓለማየሁ ራስ ወዳድ ሆኖ ካመከነው አስቆጪው አጋጣሚ በኋላ ረዘም ላለ ደቂቃ ሙከራ ሳያደርጉ የአጋማሹ መጠናቀቂያ ላይ ግብ አግኝተዋል። ኢዮብ ዓለማየሁ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ብሩክ በየነ በደረቱ ከተቆጣጠረው በኋላ አክርሮ በመምታት አስቆጥሯል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታ ተመልሶ ብርቱካናማዎቹ ጫን ብለው በመመለስ ሙከራዎችን ካደረጉ በኋላ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። 59ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ሳጥን ገብተው ያደረጉትን ሙከራ ተከላካዮች ለማራቅ ጥረት ሲያደርጉ ብዙም ሳይርቅ ኳሱን ያገኘው አቤል ነጋሽ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶ ወደ ግብነት ቀይሮ ወደ ጨዋታ መልሷቸዋል። በሊጉ ለመቆየት እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጥቃት ሲፈፅሙ የነበሩትም እነሱ ሲሆን ጥረታቸው ፍሬ ሳያፈራ ተጨማሪ ግብ ሳያገኙ ጨዋታው ተጠናቆ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዳቸውን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ መድን ከ ምድረገነት ሽረ
በሊጉ ለመቆየት የሞት ሽረት የሚያርጉትን ምድረገነት ሽረን ከኢትዮጵያ መድን ያገናኘው ሁለተኛው ጨዋታ በኳስ ቁጥጥር ብልጫ በሽረዎች ስር ሆኖ ሙከራዎችንም አድርገዋል።

ሽመክት ጉግሳ በመድን ተከላካዮች ስህተት መነሻ የተገኘችውን ኳስ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀም ከቀረ በኋላ 30ኛው ደቂቃ ላይ መሪ የሆኑበትን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ ራቅ ካለ ቦታ የቆመ ኳስ አግኘተው አዲሱ ተስፋዬ ቀጥታ ወደ ግብ በመምታት መረብ ላይ አሳርፎ ቀዳሚ እንዲሆኑ ካስቻላቸው ከአምስት ደቂቃ በኋላ ተጨማሪ ግብ ማግኘት ችለዋል። 35ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ከመስመር ያሻማውን ኳስ ዳንኤል ዳርጌ በግንባር ገጭቶ አስቆጥሮታል።

የጨዋታ ብልጫ የተወሰደባቸው መድኖች ከግቦቹ በኋላ ወደ ጨዋታ ለመመለስ ሙከራዎችን ያደረጉ ሲሆን ወገኔ ገዛኸኝ ከሳጥን ውጪ አድርጎ ለጥቂት ከፍ ያለበት እና በግንባር ገጭቶ ያደረጉትን ሙከራ ናትናኤል ከግብ መስመር የመለሰባቸው ሙከራ ወደ ጨዋታ ተመልሶ አጋማሹን እንዲጨርሱ ሊያደርጋቸው የቀረበ ቢሆንም አጋማሹ ተገባዶ ለእረፍት ወጥተዋል።
ጨዋታው ሲመለስ ወደፊት በመሄድ የተመለሱት ሽረዎቹ በፈጣን ሽግግር ሦስተኛውን ግብ አግኝተዋል። ናትናኤልን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አቤል ማሙሽ የረጅሙ ከተከላካይ ጀርባ የተጣውን ኳስ በፍጥነት ደርሶ ግብ ጠባቂው መውጣቱን አይቶ ከፍ አድርጎ በማሻገር በመጀመሪያ ንክኪው ግሩም ተጨማሪ ግብ አስቆጥሮ ለቡድኑ እፎይታ መስጥት ችሏል።

ወደጨዋታ ለመመለስ አብዝቶ ወደፊት ይሄዱ የነበሩት መድኖች በተደጋጋሚ ፈጣን ሽግግሮችን በማድረግ ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል። ሆኖም ግን ነጥቡን ይዞ መውጣት አማራጭ የሌለው ምርጫቸው የሆነባቸው ሽረዎች መከለካሉ ላይ አተኩረው ግብ እንዳይቆጠርባቸው በማድረጋቸው ሌላ ግብ ማየት አልቻልም። ጨዋታውም ለሽረዎች በሊጉ ለመቆየት ተስፋ የሰጣቸውን ወሳኝ ድል በማስገኘት ተቋጭቷል።

