ሲዳማ ቡና ባልተሟላ ስብስቡ ዝግጅቱን ቀጥሏል

ሲዳማ ቡና ባልተሟላ ስብስቡ ዝግጅቱን ቀጥሏል

በዚህ ወር መጨረሻ ኢትዮጵያን ወክሎ በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር የሚሳተፈው ሲዳማ ቡና የቅድመ  ውድድር ዝግጅቱን ከጀመረ አራተኛ ቀን አስቆጥሯል።

የ2018 የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ውድድር ሀገራችን የሚወክለው ሲዳማ ቡና የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን ከቻዱ ክለብ ኤግሎንስ ጋር መደልደሉ ይታወሳል። ለዚህም ጨዋታ ይረዳው ዘንድ በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ የሚመራው ቡድኑ ከአራት ቀናት በፊት በመቀመጫ ከተማው ሀዋሳ በቀን ሁለት ጊዜ እየሠራ መሆኑ ይታወቃል።

አራተኛ ቀኑን ባስቆጠረው የዛሬው የማለዳው ልምምድ ቡድኑ ባልተሟላ ስብስብ መጀመሩን አስተውለናል። ከታዳጊ ቡድን ያደጉት ተጫዋቾች እና ጥቂት የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋቾች በዝግጅቱ ገብተው እየሠሩ ሲሆን የተቀሩት አብዛኛው የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋቾች ይህን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ቡድኑ ያልተቀላቀሉ ቢሆኑም በቀጣዮቹ ቀናት ስብስቡን በመቀላቀል ዝግጅታቸውን አጠናክረው ይሠራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሲዳማ ቡናዎች ከነሐሴ 29 እስከ ጳጉሜ 1 ባሉት ቀናት የመጀመርያ ጨዋታቸውን ከሜዳ ውጭ የሚያደርጉ ይሆናል።