ጦሩ የጥምር ዜግነት ባለቤት የሆነውን አጥቂ የግሉ አድርጓል

ጦሩ የጥምር ዜግነት ባለቤት የሆነውን አጥቂ የግሉ አድርጓል

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው መቻል ባለልምዱን አጥቂ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።

በቀጣዩ የውድድር ዓመት ራሱን በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ለማግኘት ከአሠልጣኝ ቅጥር ጀምሮ ቡድኑን እያጠናከረ የሚገኘው መቻል ከግብ ጠባቂ እስከ አጥቂ መስመር ድረስ አዳዲስ ተጫዋቾችን እያመጣ ሲሆን በዛሬው ዕለትም የፊት መስመሩን የዩጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን ጥምር ዜግነት ባለው ቁመታም አጥቂ አጠናክሯል።

ቡድኑን የተቀላቀለው ተጫዋች ቲቶ ኦኬሎ ነው። ቲቶ ኦሌሎ በዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ቻይና/ማኩ (በቻይና ደቡባዊ የባህር ዳርቻ ላይ የሚገኝ ልዩ የአስተዳደር ክልል) ፣ ኬኒያ፣ ኢራን እና ኢንዶኔዥያ ሀገራት የተጫወተ ሲሆን ያለፈውን የውድድር ዓመት ደግሞ በሊቢያ ሊግ ተጫውቶ አሳልፏል።

በደቡባዊ የዩጋንዳ ክፍል የተወለደው ባለ ልምዱ ቲቶ ኦኬሎ ከስድስት ዓመታት በፊት ለደቡብ ሲዳን ብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት ለመስጠት ምርጫውን አድርጎ በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች ብሔራዊ ቡድኑን እያገለገለ ይገኛል። በአፍሪካ እና ኤዥያ የተለያዩ ክለቦች ተዟዙሮ የተጫወተው ባለልምዱ አጥቂ አሁን መዳረሻው መቻል ሆኖ የአንድ ዓመት ውል ፈርሟል።