“ሴኔጋል ቀድማ ካስቆጠረች ታሸንፋለች ፤ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ 30 ደቂቃዎችን መቋቋም ከቻለች ሴኔጋል ያበቃላታል” ፔፔ ሰይዶ
በኢትዮጵያ ስኬታማ የእግርኳስ ሕይወቱን እየመራ የሚገኘው ሴኔጋላዊው ተጫዋች ስለነገው ጨዋታ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

በውቡ ባሕር ዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም የሚደረገው የነገው የኢትዮጵያ እና ሴኔጋል ጨዋታ እጅግ በጉጉት እየተጠበቀ ይገኛል። ሶከር ኢትዮጵያም በተከታታይ ጨዋታውን የተመለከቱ መረጃዎች እያደረሰች የምትገኝ ሲሆን ያለፉትን ዓመታት በኢትዮጵያ እግርኳስ ስኬታማ ቆይታ እያደረገ የሚገኘውና የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዓመቱ ምርጥ ግብ ጠባቂ ፔፔ ሰይዶ ሀገሩ ሴኔጋል ከኢትዮጵያ ጋር የምታደርገውን ጨዋታ በተመለከተ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ተከታዮን ቆይታ አድርጓል።
የነገው የኢትዮጵያ እና ሴኔጋል ጨዋታ ምን አይነት ፍልሚያ ይሆናል ብለህ ታስባለህ?
“በጣም ጠንካራ እና ታክቲካል ጨዋታ ይሆናል ብየ እጠብቃለሁ። እንደሚታወቀው ሴኔጋል ከሞዛምቢክ ጋር ነጥብ ተጋርታ ነው የመጣችው ፤ ኢትዮጵያም ደግሞ በሜዳዋ ባሕርዳር ላይ በጣም ጠንካራ ናት። የአየር ንብረቱ እና ደጋፊዎች ትልቅ ልዩነት ይፈጥራሉ። እናም 90 ደቂቃው በጣም ጠንካራ ይሆናል።”
የቪየራን የመጀመሪያ ጨዋታ ተመልክተሃል? የቡድኑ ጠንካራና ደካማ ጎን ምንድን ነው?
“የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ከሞዛምቢክ ጋር ሲጫወት ጨዋታውን ተመልክቼዋለው። በተወሰነ መንገድ የቪየራን ሀሳብ ለመታዘብ ሞክሬያለሁ። ቡድኑ ከኋላ ጀምሮ ኳስ መስርቶ ለመውጣትና ኳሱን ተቆጣጥሮ ለመጫወት ይሞክራል። ፈጣን ተጫዋቾችም ስላሉ ቡድኑ ፈጣን ነው። የቡድኑ ደካማ ጎን በመከላከል ወቅት ያለው ሽግግር እና አጨራረስ ላይ ነው። እርግጥ ቡድኑ ገና እየተገነባ ነው። ጊዜ ይፈልጋል። ተጫዋቾቹም የአሠልጣኙን ሀሳብ በደንብ መረዳት አለባቸው። አዲስ ቡድን ሲገነባ ጊዜ ያስፈልጋል።”
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንቅስቃሴንስ እንዴት ታየዋለህ?
“የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በደንብ እየተሻሻለ ነው። ቴክኒካል ተጫዋቾች አሉ። ኳሱን በደንብ ይዞ መጫወት ላይ ጥሩ ናቸው። በተለይ በሜዳቸው ሲጫወቱ አደገኞች ናቸው። ቡድኑ በሱዳን ተሸንፎ ስለመጣ በውጤት ጥማት ጨዋታውን ያደርጋል ብዬ አስባለው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን መናቅ ልክ አይደለም።”
ሴኔጋላዊ ነህ ግን ደግሞ ኢትዮጵያን በጣም እንደምትወድ ደጋግመህ ስትናገር ይሰማል። ሳትደብቅ ንገረኝ! ነገ የማን ደጋፊ ነህ?
“100% ልቤ ሚለኝ የቴራንጋ አናብስት እንደሚያሸንፉ ነው። ነገርግን ለኢትዮጵያ ትልቅ ክብር አለኝ። ይቺ ሀገር ሁሉንም ነገር ሰጥታኛለች። ሴኔጋልን እየደገፍኩ ኢትዮጵያንም አከብራለሁ።”
አሁን ከቡድንህ ባህር ዳር ጋር ዝግጅት ላይ እንዳለህ ይታወቃል። ባህር ዳር ሄደህ ጨዋታውን መከታተል አላሰብክም?
ማክሰኞ ባሕርዳር ስታዲየም ላይ እገኛለሁ። እዛ ያለውን ስታፍ እና ስታዲየም አውቀዋለሁ። ስታዲየም ለመጫወት ባይሆንም ሀገሬ ከሁለተኛ ሀገሬ ጋር ስትጫወት ለማየት እገኛለሁ።
የነገውን ጨዋታ ማን ያሸንፋል ብለህ ታስባለህ?
ወረቀት ላይ ሴኔጋል ጠንካራ ስብስብ አላት ነገር ግን እግርኳስ ባሕርዳር ላይ ይለያል። የአየር ንብረት ፣ ሜዳ ፣ ደጋፊዎች…። ሴኔጋል ቀድማ ካስቆጠረች ታሸንፋለች ፤ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ 30 ደቂቃዎችን መቋቋም ከቻለች ሴኔጋል ያበቃላታል። ባሕርዳር ላይ በጣም አስቸጋሪ ጨዋታ እንደሚሆን ተስፋ አድርጋለሁ።
ከሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን በጣም የምትቀርበው ጓደኛህ የሆነው ተጫዋች ማነው?
አዎ! ብዙ ጓደኞች አሉኝ። በአካዳሚዎች አብረን ያደግን ልጆች አለን። እከሌ እከሌ ማለት ባልፈልግም ከብዙዎቹ ጋር እንቀራረባለን። በተለይ ከግብ ጠባቂዎቹ እና ተከላካዮቹ ጋር እንቀራረባለን። እንደ ጓደኛም መልካም ዕድልም እመኝላቸዋለው።
ለኢትዮጵያውያን ማለት የምትፈልገው ነገር ካለ…?
ለሁሉም ነገር ኢትዮጵያዊያንን ማመስገን እፈልጋለው። በተለይ ለቡድኔ የባህር ዳር ደጋፊዎች ትልቅ ምስጋና አለኝ። በማክሰኞውም ጨዋታ ጥሩ ነገር እንዲገጥማቸው እመኛለው። የተሻለው ቡድን እንዲያሸንፍ እመኛለው።

