👉 ለነገው ጨዋታ በሙሉ ዝግጅት እንገኛለን
👉 ጎል ለማስቆጠር አጥቅተን እንጫወታለን
👉 የድሬዳዋ ህዝብ በነቂስ ወጥቶ ይደግፈናል

በ2028 በሎስ አንጀለስ ለሚሰናዳው የኦሊምፒክ የሴቶች እግርኳስ ውድድር ላይ ተሳታፊ ለመሆን በሁለተኛው ዙር ማጣሪያ የመጀመርያ ጨዋታ ከሜዳቸው ውጭ ሩዋንዳን 1 ለ 0 በመርታት ወደ ቀጣዮ ዙር የማለፍ ዕድላቸውን አስፍተው የተመለስቱ ሉሲዎቹ በነገው ዕለት የመልስ ጨዋታ
ያከናውናሉ። በዛሬው ዕለትም የቡድኑ አሰልጣኝ ቻለው ለሜቻ ለመገናኛ ብዙሀን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
መግቢያ ንግግራቸው እንዳነሱት ከሆነ “ከመጀመርያው ጨዋታ የነበሩብን ጥቂት ክፍተቶችን ማሻሻያ ለማድረግ ከሩዋንዳ ከመጣን በኋላ ባሉት አጭር ቀናቶች ስንዘጋጅ ቆይተናል። ለነገው ጨዋታ በሙሉ ዝግጅት ላይ እንገኛለን” ብለዋል። በተጨማሪም “የመጀመርያው ጨዋታ ላይ በራስ ላይ በተቆጠረ ጎል ማሸነፋችን ይታወቃል። በምንም መንገድ ጎሎች ቢቆጠሩ ዋናው ጎል ማስቆጠራችን ነው። ይህም በተቃራኒ ቡድን የሜዳ ክፍል ላይ መድረሳችን አንድ ጥንካሬ ነው። አሁን በሜዳችን ብዙ ማግባት ይጠበቅብናል ያንን ለማድረግ የሚያስችል ስራ ሰርተናል” ብለዋል።
ከሜዳ ውጭ ጥሩ ውጤት ይዘው እንደመጡ አንስተው በነው ጨዋታ አሸንፈናል ብለው እንደማይከላከሉ ሲገልፁ” ነገ በሙሉ አቅማችን ማጥቃትን እናስባለን ለእዛ የሚሆን በቂ ዝግጅት አድርገናል። ጎል ለማስቆጠር አጥቅተን እንጫወታለን” በማለት አንስተዋል።
በማስከተል ከጉዳት ላይ በሚገኙት ሁለት ተጫዋቾች ጋር ተያይዞ ሲመልሱ “በመጀመርያው ጨዋታ ላይ ጉዳት ያጋጠማቸው ንግስት በቀለ እና አንበሏ ግብጠባቂዋ ታሪኳ በርገና ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው ምክንያት ለነገው ጨዋታ የመድረስ ዕድላቸው በጣም ጠባብ እንደሆነ” ገልፀዋል።
በመጨረሻም መልዕክታቸው “የድሬዳዋ ህዝብ እግርኳስ ወዳድ መሆኑ የሚታወቅ ነው። ነገ ህዝቡ በቂስ ወጥቶ እንዲደግፈን ጥሪዬን አስተላልፋለው” ብለዋል።

