የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ሲቀጥሉ ሲዳማ ቡና ኤሌክትሪክ ላይ ጣፋጭ ድል ተጎናፅፏል፡፡ በኢትዮጵያ ቡና እና ሀዋሳ ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ ደግሞ በደጋፊዎች ስርአት አልበኝነት ምክንያት ሁለተኛው አጋማሽ ሳይካሄድ ተቋርጧል፡፡
በ09፡00 ሲዳማ ቡናን ያስተናገደው ኤሌክትሪክ 5-0 በሆነ ሰፊ ውጤት ተረምርሟል፡፡ ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውዝጥ የሚገኘው ኤሌክትሪክ የቅርብ ተፎካካሪዎቹ ዳሽን ቢራ እና አርባምንጭ ከተማ ትላንት ነጥ በመጣላቸው መልካም አጋጣሚን ማግኘት ቢችልም ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ ይልቁንም በሲዳማ ቡና ሙሉ የጨዋታ የበላይነት ተወስዶበት ተሸንፏል፡፡
የሲዳማ ቡናን የመክፈቻ ግብ በረከት አዲሱ ከማዕዘን ምት የተሸገረውን ኳስ በመጠቀም ሲያስቆጠር የመጀመርያው አጋማሽም በ1-0 ውጤት ተጠናቋል፡፡ ከእረፍት መልስ ይበልጥ ተጠናክረው የቀረቡት ሲዳማ ቡናዎች በፍፁም ተፈሪ ሁለተኛውን በዘነበ ከበደ ግሩም ቅጣት ምት ሶስተኛውን ሲያስቆጥሩ ፈጣኑ የመስመር አማካይ አዲስ ግደይ የመጨረሻዎቹን ሁለት ግቦች አክሏል፡፡
11፡30 ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከ ሀዋሳ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በእረፍት ሰአት በተፈጠረ የደጋፊዎች ረብሻ ምክንያት ጨዋታው እንዲቋረጥ ተወስኗል፡፡ በጥሩ ድባብ እና ፈጣን እንቅስቃሴ የተጀመረው ጨዋታ በሜዳ ላይ ጉሽሚያዎች ታጅቦ ቀጥሎ ከ30ኛው ደቂቃ በኋላ መልኩን ቀይሯል፡፡ ደስታ ዮሃንስ ያሻማውን ቅጣት ምት ጋዲሳ መብራቴ አግኝቶ ወደ ግብ ሲመታ አቅጣጫው ቀይሮ አስቻለው ግርማ ጋር ሲደርስ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና ተጫዋች ወደ ግብነት ቀይሯታል፡፡ ለግቧ መቆጠር ምክንያት የነበረው ጋዲሳ መብራቴ ከጨዋታ ውጪ በሆነ አቋቋም ላይ እንደነበር በመግለፅ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በእለቱ ዳኛ ላይ ተቃውሞዋቸውን ያሰሙ ሲሆን የፕላስቲክ ጠርሙሶች ወደ ሜዳ መወርወር ጀምረዋል፡፡ አንድ ደጋፊም አጥር ዘሎ በመግባት የእለቱን አርቢቴር ለመደብደብ ሲጋበዝ ተስተውሏል፡፡
ከግቡ መቆጠር በኋላ የተቋረጠው ጨዋታ ከ7 ደቂቃዎች በኋላ በድጋሚ እንዲጀመር ተደርጎ የመጀመርያው አጋማሽ ቢጠናቀቅም በሚስማር ተራ የሚገኙ ደጋፊዎች የተሰቀሉ ባነሮችን በመቀዳደድ የጀመሩት ረብሻ በሁሉም የስታድየሙ ክፍል ተዳርሶ ከፍተኛ ትርምስ ተፈጥሯል፡፡ በፌዴራል ፖሊሶች እና በደጋፊዎች መካከል ግጭቶች የነበሩ ሲሆን በስታድየሙ የተመደበው የፀጥታ ሃይል ከነበረው የደጋፊ ብዛት ጋር ተመጣጣኝ ያልነበረ መሆኑ ችግሩን ሲያባብሰው ተስተውሏል፡፡ ሁከቱ በፈጠረው ትርምስ ምክንያትም በርካታ ደጋፊዎች እና የፀጥታ አካላት ተጎድተዋል፡፡ በወንበሮች እና በተሰቀሉ ባነሮች ላይም ጉዳት ደርሷል፡፡
ለ1 ሰአት ያህል ከቀጠለው ትርምስ በኋላ ደጋፊዎች ከስታድየሙ እንዲለቁ ተደርጎ በባዶ ስታድየም ጨዋታው እንዲቀጥል ተጫዋቾች ከመልበሻ ክፍል ቢወጡም የአለቱ ኮሚሽነር ጨዋታው እንዲቋረጥ አዘው የሁለተኛው አጋማሽ ሳይካሄድ ቀርቷል፡፡ ሁለተኛው አጋማሽ መቼ እንዲቀጥልም ከውሳኔ ላይ አልደረሰም፡፡
የኢትዮጵያ እግርኳስ በዚህ አመት ቁጥሩ የበዛ የደጋፊዎች ግጭት እና ረብሻ ማስተናገዱን ቀጥሏል፡፡ ችግሩም መፍትሄ ሳይገኝለት ከእለት ወደ እለት ስር እየሰደደ መጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሽን እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ቀላል ቅጣቶችን ከማስተላለፍ እና ጣት ከመቀሳሰር ባለፈ የማያዳግሙ የመፍትሄ እርምጃዎች ካልተሰዱ በቀር እየተባባሰ የመጣው የደጋፊዎች ረብሻ ከእግርኳስ ሜዳዎች አልፎ ትልቅ ሃገራዊ ስጋት ወደመሆን መሸጋገሩ አይቀሬ ነው፡፡