የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ከ20 አመት በታች ዋንጫ ማጣርያ ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ ዛሬ ከጋና ጋር ወሳኝ የመልስ ጨዋታውን ያካሂዳል፡፡
የቡድኑ አሰልጣኝ ግርማ ሃብተዮሃንስ በጨዋታው ተያያዥ ጉዳዮች ዙርያ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ያደረጉትን ቆይታ እነሆ ብለናል፡፡
ጉዞ
አአ የወጣነው እሁድ ነው እስካሁን በሆቴል በመስተንግዶ በጉዞ ያጋጠመን የከፋ ችግር ባይኖርም በተወሰነ መልኩ ከማሊ – ጋና – አክራ – ኬፕ ኮስት (የምንጫወትበት ከተማ) ረጅም ጉዞ አጋጥሞን ነበር፡፡ ከዚህ አድካሚ ጉዞ በቀር የጎላ ችግር አላጋጠመንም፡፡ የአየር ንብረቱም እንደ አአ ባይሆንም ወበቃማ ንፋስ የተቀላቀለበት ነው፡፡ በአጠቃላይ ሁሉ ነገር ጥሩ ነው፡፡
ስለ ልምምዳቸው
ጋና ከገባን ጀምሮ ዋና መወዳደርያ በምንጫወትበት ሜዳ ላይ አንድ ጊዜ በአጠቃላይ ወደ አራት የሚጠጉ የልምምድ ጊዜዎችን በሚገባ አሳልፈናል፡፡ በተጨማሪ ከጋና ጋር የመጀመርያው ጨዋታና ከማሊ ጋር በነበረን ጨዋታ ዙርያ በቪዲዮ በማሳየት ማረም የሚገቡንን ድክመቶቻችን ላይ ተወያይተናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሀገሪቱን የሊግ ጨዋታ ሜዳ በመሄድ እንዲከታተሉ በማድረግ የተመልካቹን አደጋገፍና የአጨዋወት ባህርያቸውን በመመልከት ዛሬ አዲስ እንዳይሆኑ የማዘጋጀት ስራ ሰርተናል፡፡
የማሊው ሽንፈት
የማሊው ጨዋታ የሚያሳድርብን ተፅእኖ የለም፡፡ ነገር ግን እንድንጠነቀቅ እና ትኩረት እንዲኖረን ተጫዋቾቻችን ትኩረታቸውን ሳይቀንሱ ንቁ ሆነው መጫወት እንዳለባቸው አስገዝቦናል እንጂ ሞራል የሚጎዳ ቅስም የሚሰብር ተስፋ የሚያስቆርጥ አይደለም፡፡ እንዲያውም ጥሩ ትምህርት አግኝተንበታል ፤ ተቀራራቢ ሀገሮች በመሆናቸው አጨዋወታቸው ተመሳሳይ ነው፡፡ ሜዳውን
በጣም ለጥጠው ነው የሚጫወቱት ፤ የጉልበት እና ረጅም ኳስ ላይ ትኩረት ያደርጋሉ፡፡ ይህን አጨዋወት ለመታዘብ ችለናል፡፡
የቡድን መንፈስ
ተጫዋቾቹ በጥሩ መንፈስ ላይ ናቸው ፤ ለጨዋታውም በሚገባ ተዘጋጅተዋል፡፡ የሚጫወቱትንም 18 ተጨዋች ለይተናል፡፡ ሱራፌል አወል ባጋጠመው ጉዳት ከ18 ውጭ ከመሆን በስተቀር ሁሉም በሙሉ ፍላጎት ፣ ሞራል እና ጤንነት ላይ ይገኛሉ፡፡
** ብሄራዊ ቡድኑ ከተጓዙበት ዕለት አንስቶ ጋዜጠኛ ዘርአይ እያሱ ፎቶና መረጃዎችን እንድናገኝ በማመቻቸት ላደረገልን ከፍተኛ እገዛ ሶከር ኢትዮዽያ ታመሰግናለች፡፡