በግብፅ ፕሪሚየር ሊግ 32ኛ ሳምንት አል ስዊዝ ስታድየም ላይ ምስር አል ማቃሳን ያስተናገደው ፔትሮጄት 3-2 ማሸነፍ ችሏል፡፡ በጨዋታው ቋሚ የነበረው ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ሽመልስ በቀለ ሶስቱንም የድል ግቦች አስቆጥሮ ሐት-ትሪክ በመስራት ደምቆ አምሽቷል፡፡
በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ የሚገኘው ፔትሮጄት እና በአል-አህሊ ትሪፖሊ ተሸንፎ ከካፍ ኮንፌዴሬሽን ከተሰናበተ በኋላ መንሸራተት ባሳየው ምስር አል ማቃሳ መካከል የተካሄደው ጨዋታ እልህ አስጨራሽ ፉክክር ተካሂዷል፡፡
ሽመልስ ከኦሳማ መሃመድ የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ፔትሮጄትን ቀዳሚ ማድረግ ሲችል በ51ኛው ደቂቃ ሁለተኛውን አክሎ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ማስፋት ችሏል፡፡
የፋዩም ከተማ ክለብ የሆነው ምስር አል -ማቃሳ በቀድሞው የዋይዳድ ካዛብላንካ አማካይ ኦማር ናጅዲ የ61ኛ ደቂቃ ግብ ልዩነቱን ማጥበብ ሲችል ከ12 ደቂቃዎች በኋላ ኦማር በድጋሚ ግብ አስቆጥሮ ማቃሳን አቻ ማድረግ ችሎ ነበር፡፡ ጨዋታው ሊጠናቀቅ 4 ደቂቃዎች ብቻ ሲቀሩ የምሽቱ ኮከብ ሽመልስ በቀለ ወሳኟን የማሸነፍያ ግብ ከመረብ አሳርፎ ፕትሮጄትን ለድል አብቅቶታል፡፡
በ2014 የውድድር ዘመን በሱዳን ቆይታው ለአል ሜሪክ በአንድ ጨዋታ 5 ግቦች በማስቆጠር ታሪክ ሰርቶ የነበረው ሽመልስ በቀለ ትላንት ሐት-ትሪክ መስራቱን ተከትሎ በግብፅ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ ሐት-ትሪክ የሰራ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ በመሆን ታሪክ አስመዝግቧል፡፡
ሊጉን አል አለህሊ በ71 ነጥቦች ሲመራ የምንግዜም ባላንጣው ዛማሌክ በ66 ነጥቦች ይከተላል፡፡ 43 ነጥቦች የሰበሰበው ፔሮጄት 10ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ከጋዛል ኤል ማህሳ ጋር ያለ ግብ የተለያየው የኡመድ ኡኩሪው ኢኤንፒፒአይ ከፔትሮጄት በ2 ነጥቦች ዝቅ ብሎ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡