የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 20 ሳምንት ቀሪ ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ ጅማ አባ ቡና እና ፋሲል ከተማ መሪነታቸውን ያጠናከሩበትን ድል ከሜዳቸው ውጪ አስመዝግበዋል፡፡
በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውና በደረጃ ሰንጠረዡ 1ኛ እና 2ኛ ላይ ተቀምጠው የነበሩት ጅማ አባ ቡና እና አዲስ አበባ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በጅማ አባ ቡና የበላይነት ተጠናቋል፡፡ ከወትሮው በተለየ መልኩ በአበበ ቢቂላ በርካታ ተመልካቾች የተገኙ ሲሆን የሁለቱም ቡድን ደጋፊዎች የክለቦቻቸውን አርማ በመያዝ ቡድኖቻቸውን ሲያበረታቱ ታይተዋል፡፡
ጨዋታው በተጀመረ 8ኛው ደቂቃ ላይ አሜ መሃመድ የተከላካዮችን ስህተት ተጠቅሞ ብቸኛዋን የማሸነፍያ ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ከግቡ መቆጠር በኋላ አዲስ አበባ ከተማዎች ሙሉ ለሙሉ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ቢይዙም የግብ እድ መፍጠር ላይ እምብዛም ሆነው ውለዋል፡፡ የጅማ አባ ቡና የተከላካይ ክፍልም ለአባ ቡና ድል ትልቁን ሚና ተወጥተዋል፡፡ በተለይም የመሃል ተከላካዩ ሂደር ሙስጠፋ ያሳየው አቋም በስታድየሙ የተገኘውን ተመልካች አስደንቋል፡፡ ከድሉ በኋላም የጅማ አባ ቡና ቡድን አባላት ወደ ደጋፊዎቻቸው በመሄድ ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡
ድሉን ተከትሎ በውድድር ዘመኑ አንድም ሽንፈት ያላስተናገደው ጅማ አባ ቡና በ45 ነጥቦች መሪነቱን ሲያጠናክር አዲስ አበባ ከተማ በ7 ነጥቦች ርቆ ተከታዩን ደረጃ ለመያዝ ተገዷል፡፡
ወደ መድን ሜዳ ያቀናው ፋሲል ከተማ ሙገር ሲሚንቶ ላይ ድል አስመዝግቦ መሪነቱን ማጠናከር ችሏል፡፡ በርካታ ደጋፊዎች በተገኙበት ጨዋታ አቡበከር ደሳለኝ ጨዋታው በተጀመረ ገና በ4ኛው ደቂቃ የአፄዎቹን ብቸኛ የድል ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡ ተጫዋች ለህክምና እርዳታ ወድቆ ኳሱ ወደ ውጭ ይወጣል ተብሎ ሲጠበቅ ፋሲሎች ግብ ማስቆጠራቸው ሙገር ሲሚንቶ ላይ ቅሬታን ፈጥሯል፡፡ ክስም አስመዝግዋል፡፡
በጨዋታው የፋሲል ከተማው ግብ ጠባቂ ተስፋዬ በቃና በፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ በዳሶ ሆራ ላይ ጥፋት በመስራቱ የቀጥታ ቀይ ካርድ ሰለባ ሲሆን የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት እስክንድር አብዱልሃሚድ መትቶ የግቡ ቋሚ መልሶበታል፡፡ አመዛኙን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በጎዶሎ ተጫዋች የተጫወቱት ፋሲሎች በመጨረሻም ወሳኙን ነጥብ አሳክተዋል፡፡
ውጤቱ ፋሲል ከተማ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ለሚያደርገው ጉዞ ወሳኝ ድ ሆኖ ሲመዘገብ ሙገር ሲሚንቶ ማሽቆልቆሉን ቀጥሎ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ለመቆየት ተገዷል፡፡
የከፍተኛ ሊጉ 20ኛ ሳምንት ነገ በሚደረግ ጨዋታ ሲገባደድ በምድብ ለ ደቡብ ፖሊስ ሀላባ ከተማን ያስተናገዳል፡፡ እረፍት ሰአት ላይ የተቋረጠው የወልድያ እና አማራ ውሃ ስራ ጉዳይም በቀጣዮቹ ቀናት ፌዴሬሽኑ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ቀጣይ ጨዋታዎች
ምድብ ሀ
ቅዳሜ ሰኔ 11 ቀን 2008
09፡00 ወልድያ ከ መቐለ ከተማ (ወልድያ)
09፡00 አማራ ውሃ ስራ ከ አክሱም ከተማ (ባህርዳር)
09፡00 ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከ ባህርዳር ከተማ (አዲግራት)
09፡00 ኢትዮጵያ መድን ከ ሰሜንሸዋ ደብረብርሃን (መድን ሜዳ)
09፡00 ቡራዩ ከተማ ከ ወሎ ኮምቦልቻ (ቡራዩ)
09፡00 ሰበታ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ውሃ ስፖርት (ሰበታ)
ማክሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2008
09፡00 ፋሲል ከተማ ከ ሱሉልታ ከተማ (ጎንደር)
10፡00 አዲስ አበባ ፖሊስ ከ ሙገር ሲሚንቶ (አበበ ቢቂላ)
ምድብ ለ
አርብ ሰኔ 10 ቀን 2008
09፡00 ፌዴራል ፖሊስ ከ ጂንካ ከተማ (አበበ ቢቂላ)
ቅዳሜ ሰኔ 11 ቀን 2008
08፡00 አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ ጅማ ከተማ (አበበ ቢቂላ)
09፡00 ወራቤ ከተማ ከ ሻሸመኔ ከተማ (ወራቤ)
09፡00 አርሲ ነገሌ ከ ድሬዳዋ ፖሊስ (አርሲ ነገሌ)
09፡00 ነገሌ ቦረና ከ ደቡብ ፖሊስ (ነገሌ ቦረና)
10፡00 ናሽናል ሴሜንት ከ ባቱ ከተማ (ድሬዳዋ)
ማክሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2008
09፡00 ጅማ አባ ቡና ከ ነቀምት ከተማ (ጅማ)
ረቡዕ ሰኔ 15 ቀን 2008
09፡00 ሀላባ ከተማ ከ አዲስ አበባ ከተማ (ሀላባ)