“በትንሽ ነገር ውስጤ የሚጎዳ ባለመሆኑ ጠንክሬ ሠርቼ እዚህ ደርሻለሁ” – መሐሪ መና

ከአንድ ዓመት ጉዳት በኋላ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ሲዳማ ቡናን ተቀላቅሎ ጥሩ ጊዜ ያሳለፈው መሐሪ መና ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።

በአንጋፋው አሰልጣኝ ጋሽ ከማል አህመድ ስር በታዳጊነቱ ተጫውቶ ካለፈ በኃላ በሀዋሳ ከተማ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመቀጠል ረጅሙን የእግርኳስ ህይወቱን ወደ መራበት ቅዱስ ጊዮርጊስ በማቅናት ለስድስት ዓመት ቆይታ አድርጎ አራት የሊግ ዋንጫ ጨምሮ ሌሎች ድሎችን አጣጥሟል። በ2011 ሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስታዲየም መከላከያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረጉት የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍፃሜ ጨዋታ ወቅት ጉልበቱ ላይ ከበድ ያለ ጉዳት አስተናግዶ ለአንድ ዓመት ከሜዳ ርቆ ቆይቷል። መሐሪ ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ጨዋታ በተመለሰበት ቅፅበት የኮሮና ወረርሺኝ በሀገራችን ስጋት ሆኖ ውድድሮች መሰረዛቸው በእግርኳስ ህይወቱ ላይ ፈታኝ ነገሮች ተከስተዋል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከተለያየ በኃላ ሌሎች ክለቦች ለማስፈረም ፍላጎት ቢኖራቸውም ጉዳት አለብህ በማለት ሳያስፈርሙት መቅረቱ ከባድ ጊዜ እንዲያሳልፍ እንዳደረገው ይናገራል። መሐሪ አሰልጣኝ ገብረመድኅን አምኖበት በማስፈረሙ አሁን ላለበት ደረጃ ትልቅ አስተዋፆኦ መኖሩንም ያምናል። በግማሽ ዓመት የዝውውር መስኮት ሲዳማ ቡና ከፈረመ በኃላ ድንቅ ጊዜን ያሳለፈው መሐሪ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረገው ቆይታ በጉዳት ምክንያት ስላሳለፈው አስቸጋሪ ጊዜ እና አሁን ስለሚገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ ሀሳቡን ሰጥቷል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ የነበረህ ቆይታ እና የገጠመህ ጉዳት እንዴት ነበር ?

ከጊዮርጊስ ጋር ስድስት ዓመት ቆይቻለሁ። በእግርኳስ ህይወቴም ደስተኛ የሆንኩባቸውን ጊዜያት አሳልፌያለሁ። ሦስት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ፣ ሁለት የጥሎ ማለፍ አንድ እና የአአ ሲቲ ካፕ እንዲሁም አንድ የሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ አንቻለሁ። በዚህ በጣም ስኬታማ ነበርኩ። ከዛ በኋላ ነው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ከመከላከያ ጋር ሀዋሳ ላይ ስንጫወት የቀኝ ጉልበቴ ላይ ጅማቴ ተበጠሰ እና በዛ የተነሳ ነው ለረዥም ጊዜ ከሜዳ በመራቄ ጊዮርጊስን መልቀቅ የቻልኩት።

የህክምናህ ሁኔታ እንዴት ነበር?

ህክምናዬን ሕንድ ነው የወሰድኩት። በሀገሪቱ አለ ወደተባለና የተሻለ ህክምና ወደሚሰጥበት ሆስፒታል ነበር የሄድኩት። ቀዶ ጥገና ሲባል ከባድ ይመስላል እንጂ በጣም ቀላል እና ዘመናዊ የሆነ ሰርጀሪ ነበር የተሰራሁት። ጥሩ ህክምና ስለሰጡኝ ነው ወደ ሜዳ ዳግም መመለስ የቻልኩት ።

ጉዳቱ ምን ያህል ጊዜ ከሜዳ አራቀህ ?

በጉዳት ከሜዳ የራኩት ወደ አንድ ዓመት አካባቢ ነው። ከዛ በኋላ ወደ ሜዳ ለመመለስ የአዕምሮ ጥንካሬ እና በቂ እረፍት ያስፈልጋል። እኔ ሀኪሞቹ የነገሩኝን በሚገባ በማድረጌ እና ጠንክሬ በመሥራቴ ነው ወደ ሜዳ መመለስ የቻልኩት ።

አሁን ላይ ያለህበትን ደረጃ ስታስበው ያሳለፍከውን አስቸጋሪ ጊዜ እንዴት ነው የምታስታውሰው ?

የጉዳት ጊዜ ከምነግራችሁ በላይ በጣም አስቸጋሪ ነበር። አንደኛ ቤተሰቦቸን ማመስገን እፈልጋለሁ፤ ከኔ ጋር ነበሩ። በተለይ እናቴ ከኔ ጋር ነበረች። ብዙ መስዋዕነት ከፍላለች። እኔም በአዕምሮ ጠንካራ ነኝ። በትንሽ ነገር ውስጤ የሚጎዳ ባለመሆኑ ጠንክሬ ሠርቼ እዚህ ደረጃ ደርሻለው። ጂም እና የማጠንከሪያ ቴራፒዎችን ስለምሰራ ነው ከጉዳቱ ወዲያው አገግሜ እንደዚህ አይነት ብቃት ላይ ልገኝ የቻልኩት ።

ጉዳትህን ስታስበው እግርኳስ ላቆም ነው ብለህ የሰጋህበት ጊዜ ነበር ?

በእርግጥ እንደዚህ እጅ የምሰጥ ሰው አይደለሁም። የሆነ ጊዜ ዝም ብዬ ሳስብ ነገ ተመልሼ እንደምመጣ አውቃለሁ። ያም ሆኖ ግን የጅማት ጉዳት ስለሆነ ፍራቻ አለ። ላቆም ነው ብዬም ሰግቻለሁ። እንዲያውም አንዴ ቤቴ ቁጭ ብዬ ብቻዬን አልቅሻለሁ። ከዛ በኋላ ተስፋ መቁረጥ የለብኝም በማለት ከራሴ ጋር ተመካክሬ የሚያስፈልጉኝን ልምምዶች መሥራት ጀመርኩ። ጂም ውስጥ በቀን ሁለቴ እየተመላለስኩ ሠራሁ። ፈጣሪ ይመስገን እግሬም ወደ ሙሉ ጤንነት ሊመጣ ችሏል።

ሲዳማ ቡናን ከመቀላቀልህ በፊት የተለያዩ ክለቦች ፍላጎት ቢያሳዩም ጥርጣሬ ነበረባቸው፤ ጉዳት ይኖርብሃል የሚል። ይህስ ምን ያህል ለአንተ ከባድ ነበር ?

እውነት ለመናገር በጣም ከባድ ነበር። እኛ ሀገር አንድ ያመንኩት ነገር ከበድ ያለ ጉዳት ስትጎዳ የምትመለስ አይመስላቸውም። በቃ በዛው ኳስ አቁመህ የምትቀር ይመስላቸዋል። ብዙ የውጭ ሀገር አሰልጣኞች አንድ ተጫዋች ቀዶ ጥገና ቢያደርግ ነገ እንደምትመጣ ያውቃሉ። በድጋሚ ሜዳ ውስጥም ገብተህ የተሻልክ መሆን እንደምትችል ስለሚያውቁ ምንም ችግር የለባቸውም። አሁን እኛ ጋር ያልተለመደ ነገር አለ ተጎዳህ ማለት የምትመለስ አይመስላቸውም። ብዙ ክለቦች በእኔ እምነት እያላቸው ለማስፈረም እየፈለጉ ድንገት ጉዳቱን እየሰሙ እየሸሹ ነበር። ይህ ለኔ በጣም ከባድ ጊዜ ነበር። ሆኖም አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ በእኔ ሙሉ እምነት ወስዶ ጠራኝ። ከዛ ሜዳ ወስጥ ሲያየኝ ጥሩ ነገር ተመለከተ። ከዛም ወዲያው ነው ኮሚቴውን ተነጋግሮ እንድፈርም ያደረገኝ። እና አሰልጣኞች ጥርጣሬ አላባቸው። ይህን ነገር መቅረፍ አለባቸው።

ሲዳማ ቡና ውስጥ ያሳየኸውን ብቃት ከሜዳ ርቀህ እንደመምጣትህ አደርገዋለው ብለህ አስበህ ነበር ?

እውነት ለመናገር እኔ ልምምድ ላይ በደንብ ነው የምሰራው። የቡድን አጋሮቼን ብትጠይቃቸው ይነግሩሃል። በቀን ሁለቴ ነው የምሰራው። ትርፍ ትሬይኒንጎችን እሰራለሁ። ጠዋት ጅም እገባለሁ። ያ ማለት ነገ የተሻለ ቦታ እንደምደርስ የተሻለ ውጤት እንደማመጣ ስለማምን ነው። ዛሬ ላይ ሆኜ ያሳየሁት ብቃት የሰራሁበት የልፋቴ ውጤት ነው።

ሲዳማ ቡና ስትመጣ ክለቡ ላለመውረድ አስቸጋሪ ጊዜ ላይ ነበር። አንተም ከጉዳት ነው የመጣኸው። እነዚህ ነገሮች ይከብዱኛል ብለህ ሰግተህ ነበር ?

ቅድም እንዳልኩት በአዕምሮ ጠንካራ ሰው ነኝ። በትንሽ ነገር ተስፋ የምቆርጥ ሰው አይደለሁም። ልክ እኔ ስመጣ እኔ ብቻ ሳይሆን ጥሩ ጥሩ የሚባሉ ተጫዋቾች ሲዳማ ቡናን ተቀላቅለው ነበር። ከዚህ የተነሳ ቡድኑ እንደማይወርድ እርግጠኛ ነበርኩ። እርግጥ ነው የተወሰኑ ጨዋታዎች ተቸግረን ነበር። ምክንያቱም አሰልጣኛችን አዲስ ቡድን እየሠራ ስለነበር ትንሽ ችግር ውስጥ ነበርን። በኋላ የተወሰነ ዕረፍት ስናገኝ የቡድኑ አባላት ተሰብስበን ተነጋገርን። ቡድኑን ማትረፍ እንዳለብን በመተማመናችን ስጋት አልነበረብኝም። ቢያንስ በደረጃ ባንከተውም ከመውረድ አደጋ እንደምናወጣው እምነት ነበረኝ።

በማጥቃትም በመከላከሉም ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል ጎልም አስቆጥረሃል። እንዴት ነው የምትገልፀው በሲዳማ የነበረህን ቆይታ?

አሁን ለሲዳማ በመጫወቴ በጣም ደስተኛ ነኝ፤ የለፋሁበትን ውጤት ነው ያገኘሁት። በጣም እሠራለሁ። ያ ነው እንግዲህ። የመመላለስ የማጥቃት የመከላከሉ ነገር በመሥራት ያገኘሁት ውጤት ነው። ከዚህ በኋላ ብዙ የምማራቸው ነገሮች አሉ። በዚህ የማበቃ ሰው አይደለሁም። በሚቀጥለው ዓመት ዘንድሮ ካሳለፍኩት የተሻለ ጊዜው ለማሳለፍ ከወዲሁ እየሰራሁ ነው። ጊዜው ሲደርስ እናየዋለን።

ዘንድሮ ሲዳማ ከመውረድ ነው የተረፈው። ቀጣይ ዓመት ሲዳማን በምን መልኩ እንጠብቀው ?

በሚቀጥለው ዓመት ምንም ጥርጥር የለውም የተሻለ እና ለዋንጫ የሚፎካከር ቡድን ነው የሚሆነው። የዘንድሮው ውድድር ዓመት እንዳለቀ ለቀጣይ ዓመት የሚያስፈራ ቡድን እንደሚሰራ ነው የተነገረን። ማንም አሁን የኛን ቡድን ሲያየው እንደሚፈራ ነው የሚሰማኝ። በቀጣይ ሲዳማ ቡና ጠንካራ ሆኖ ሊቀርብ እንደሚችል ይናገራሉ። ስለዚህ ቀጣይ ዓመት ለዋንጫ ነው የምንጫወተው። ምንም ስለ መውረድ የሚያሰጋን ነገር አይኖርም።

ከባዱን ጊዜ አልፈህ ነው እዚህ የደረስከው። ያንን ከባድ ጊዜ በምን ነበር ስታሳልፍ የነበረው ?

ምንም ስለ ህመሙ ማሰብ ስለማልፈልግ እና ፍላጎቴ ነገን ብቻ ማየት ስለሆነ ያን ነገር ከአዕምሮዬ ለማውጣት ፊልሞችን በመመልከት እና ወደ ወደ ቤተ-ክርስቲያን እየሄድኩ በመፀለይ አሳልፌያለሁ። እናቴም ካጠገቤ ነበረች፤ የሷ ፀሎት ረድቶኛል። እውነቴን ነው የምልህ አሁን ቆሜ እንድጫወት ያደረገችኝ እናቴ ናት። ለእርሷ የተለየ ክብር ነው ያለኝ። እናቴን በጣም በጣም ነው የምወዳት። እኔ ወደ ሜዳ እንድመለስ ብዙ ብዙ መስዕዋትነት ከፍላለች። በዚህ አጋጣሚ ላመሰግናት እፈልጋለሁ። እግዚአብሔር እናቴን በጤና እንዲያቆይልኝ ነው የምፈልገው።