ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | 27ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በሀዋሳ ቆይታው የመጨረሻ በሆነው የ27ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ላይ ጎልተው የወጡ ተጫዋቾችን እና አሰልጣኝን የመረጥንበት ምርጥ ቡድንን በተከታይ መልኩ አሰናድተናል።

\"\"

ግብ ጠባቂ

አቡበከር ኑራ – ኢትዮጵያ መድን

በሳምንቱ ጎልተው የወጡ ግብ ጠባቂዎችን መመልከት ባንችልም በአንፃራዊነት ኢትዮጵያ መድን ከሽንፈት ወደ ድል በተመለሰበት የኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ላይ አቡበከር ከነበረው የሜዳ ላይ መሪነት እንዲሁም በሁለተኛው አጋማሽ በአንድ ለአንድ ግንኙነት በተለይ የብሩክ በየነን ግልፅ ወደ ግብነት የምትለወጥ ኳስን የታደገበትን አጋጣሚ መነሻ አድርገን በሳምንቱ የስብስባችን አካል አድርገነዋል።

ተከላካዮች

አብዱልከሪም መሐመድ – ኢትዮጵያ መድን

ኢትዮጵያ መድን ድል በቀናው የሳምንቱ ጨዋታው ጥሩ የግብ ዕድሎችን ካገኘባቸው ተጫዋቾች መካከል የቀኝ መስመር ተሰላፊው ሚና ይልቃል። ከተጣለበት የመከላከል ኃላፊነት በተሻለ ለማጥቃት ኮሪደሩን በአግባቡ ሲሸፍን የታየበት መንገድም በምርጥነት አስመርጦታል።

በረከት ሳሙኤል – ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ከተማ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት የመጀመሪያ ድሉን ድቻ ላይ ሲያሰካ የመሐል ተከላካዩ በረከት ሳሙኤል ድርሻ ትልቁን ቦታ ይወሰዳል። የወላይታ ድቻን ተሻጋሪ ኳሶችም ሆነ በቅብብል ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ በብቃት ኳሶችን ሲያስጥል የነበረው ተከላካዩ ጥሩ የጨዋታ ቀን ማሳለፉን ተከትሎ ልንመርጠው ችለናል።

ፈቱዲን ጀማል – ባህርዳር ከተማ

ባህርዳር በተለይ በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ ተፈትኖም ቢሆን ከመቻል ሦስት ነጥብን ሲሸምት የመሐል ተከላካዩ ፈቱዲን ለቡድኑ ድል መሳካት ድርሻው ከፍ ያለ ነበር። መቻሎች ከዕረፍት መልስ የተሻሉ ሆነው በተንቀሳቀሱበት ሰዓት የአየር እና የምድር ኳሶችን በማስጣል ተጨማሪ ግቦች ተቆጥረውም ቡድኑ ውጤት እንዳያጣ ካደረገው የጎላ ድርሻ አንፃር የስብስባችን አካል ሆኗል።

ተስፋዬ መላኩ – ወልቂጤ ከተማ

ወልቂጤ ከተማ ከፋሲል ከነማ ጋር አቻ ሲለያይ ተስፋዬ በመከላከሉ ረገድ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ ነበረው። የግራ የሜዳውን ክፍል ፋሲሎች ተጠቅመው ግቦችን እንዳያስቆጥሩ ተጫዋቾችን በመቆጣጠር ያደርግ ከነበረው ትጋት አንፃር ምርጫችን ሆኗል።



አማካዮች

ሀይደር ሸረፋ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ፈረሰኞቹ መሪነታቸውን ባስቀጠሉበት ጨዋታ ላይ አምበሉ እና አማካዩ ሀይደር ቡድኑ በተጋጣሚው በተፈተነበት ጨዋታ ጥሩ የሜዳ ላይ ቆይታ ነበረው። ተጫዋቹ ከቢኒያም በላይ ጋር መሐል ሜዳ ላይ ከፈጠረው ጥሩ መናበብ እንዲሁም በራሱ አስጀማሪነት ካስቆጠራት ግብ ጥራት እና በቦታው በንፅፅር ከሌሎች ቡድኖች ተጫዋቾች የተሻለ በመሆኑ መርጠነዋል።

ወገኔ ገዛኸኝ – ኢትዮጵያ መድን

ከዕለት ወደ ዕለት ራሳቸውን በሊጉ ላይ እያደመቁ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል ወጣቱ አማካይ አንዱ ነው። በተጠናቀቀው የጨዋታ ሳምንት ከጉዳት ወደ አሰላለፍ የተመለሰው አማካዩ ሜዳ ላይ ከነበረው ድንቅ ጊዜ በተጨማሪም ቡድኑ ወሳኝ ድል እንዲያሳካ ሁለት ጎሎችን ከመረብ በማገናኘት ካደረገው አስደናቂ ተሳትፎ አንፃር በምርጥነት ልናካትተው አስችሎናል።

ቢኒያም በላይ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ በለገጣፎ ቢፈተንም ሦስት ነጥብን አግኝቶ መሪነቱን ባጠናከረበት ጨዋታው ከሚታወቅበት የመስመር ተጫዋችነቱ ወደ መሐል ገብቶ እንዲጫወት የተደረገው ቢኒያም በላይ የሜዳ ላይ ቆይታው ከፍ ያለ ነበር። በሁለቱም አጋማሾች ቡድኑ ጎል ሲያገባ ለአጎሮም ሆነ ለሀይደር ግብ መቆጠር አመቻችቶ ማቀበል መቻሉን ተከትሎ የምርጫችን አካል ተደርጓል።

አጥቂዎች

ፍፁም ጥላሁን – ባህር ዳር ከተማ

ባህር ዳር ከተማ መቻልን ሲረታ ወደ አሰላለፍ የተመለሰው ፍፁም በእንቅስቃሴም ሆነ ጎሎች እንዲቆጠሩ በማድረግ ልቆ የተገኘበት ሳምንት ነበር። ሀብታሙ ታደሠ ላስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች ኳሶችን አመቻችቶ ሲያቀል በራስ ላይ የተቆጠረችው ሦስተኛ ግብም መነሻ ከመሆኑ አኳያ ከዓሊ ሱለይማን ጋር ተፎካክሮ የተሻለ በመሆኑ ልንመርጠው ችለናል።

ሀብታሙ ታደሠ – ባህርዳር ከተማ

ባህር ዳር የሀዋሳ ቆይታውን በድል በዘጋበት ጨዋታ የፊት ተሰላፊው ድርሻ ትልቅ ነበር። የመቻልን ተከላካዮች ገና ከጅምሩ ሲረብሽ የተስተዋለው እና ፍፁም ጥላሁን የሰጠውን ሁለት ኳሶች በአግባቡ ወደ ጎልነት ከለወጠበትን ሚናው ተነስተን የስብስባችን አካል ልናደርገው ችለናል።

ሙጂብ ቃሲም – ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ በከተማው የመጀመሪያ ድሉን ሲያገኝ ከወትሮው በተሻለ ሜዳ ላይ የነበረው ሙጂብ ድርሻው ቀላል አልነበረም። በጨዋታው ከዓሊ ሱለይማን ያገኛቸውን ኳሶች ወደ ጎልነት ከመለወጡ በተጨማሪ ቡድኑን ወደ ኋላ በመመለስ ውጤቱን አስጠብቆ እንዲወጣ ሜዳ ላይ ካደረገው ተጋድሎ አንፃር ከባዬ ገዛኸኝ ጋር ተፎካክሮ የምርጫችን አካል ሆኗል።

\"\"

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

በሳምንቱ በተደረጉ ጨዋታዎች ውጤታማ ሆነው የጨረሱ አሰልጣኞች ቢኖሩም በንፅፅር የተሻለው ዘርዓይ ሙሉ የሳምንቱ ምርጥ ሊሰኝ ችሏል። ሀዋሳ ከነበረው የመልሶ ማጥቃት አቀራረብ ፣ ከተጫዋች አጠቃቀም እና ጨዋታውን ተቆጣጥሮ ከወጣበት መንገድ አኳያ ከባህርዳሩ አሰልጣኝ ደግአረገ ጋር አወዳድረን አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን መርጠናል።

ተጠባባቂ

ሚካኤል ሳማኪ – ፋሲል ከነማ
በርንድ ኦቼንግ – አርባምንጭ ከተማ
ዮሴፍ ታረቀኝ – አዳማ ከተማ
ዱሬሳ ሹቢሳ – ባህር ዳር ከተማ
ብሩክ ሙሉጌታ – ኢትዮጵያ መድን
ዓሊ ሱለይማን – ሀዋሳ ከተማ
ባዬ ገዛኸኝ – ሀዲያ ሆሳዕና