ሪፖርት | ተጠባቂው የረፋዱ ጨዋታ በቡናማዎቹ አሸናፊነት ተጠናቋል

ሪፖርት | ተጠባቂው የረፋዱ ጨዋታ በቡናማዎቹ አሸናፊነት ተጠናቋል

ቡናማዎቹን ከብርቱካናማዎቹ ያገናኘው ተጠባቂው የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች ለቡናማዎቹ ሦስት ነጥብ በማጎናፀፍ ተቋጭቷል።

ቡናማዎቹ በ26ኛው ሳምንት በሲዳማ ቡና 1ለ0 ሽንፈት ካስተናገዱበት ቋሚ አሰላለፍ ሁለት ለውጦችን አድርገው፤ ኢያሱ ታምሩን በረጀብ ሚፍታህ እና ስንታየሁ ወለጬን በአማኑኤል አድማሱ ተክተው ቀርበዋል፤ ብርቱካናማዎቹ በበኩላቸው በ26ኛው ጨዋታ ሳምንት ፋሲል ከነማን 1ለ0 ከረቱበት ቋሚያቸው የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ አቤል አሰበ፣ ሄኖክ ሀሰን እና ሐቢብ ከማልን አሳርፈው በምትካቸው ዩሐንስ ደረጄ ፣መስዑድ መሐመድ እና አቡበከር ሻሚልን ይዘው ገብተዋል።

ሁለቱን ከሽንፈት የተመለሱ ቡድኖችን ያገናኘው የጨዋታ ሳምንት የሁለተኛ ቀን የረፋዱ ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች ቀድመው ግብ ለማስቆጠር በሚያደርጉት ፈጣን በሆኑ ሽግግሮች ጋር ታጅቦ ጥሩ እንቅስቃሴ በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች አስመልክቶናል። ከ10ኛው ደቂቃ በኋላ የቡናማዎቹ አማኑኤል አድማሱ ሳጥን ውስጥ ሆኖ አከታትሎ ያደረጋቸው ሁለቱ ሙከራዎች ይጠቀሳሉ ፤ በተለየም በ12ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ ቅብብል በመግባት አማኑኤል አድማሱ ብቻውን ሆኖ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ አላዛር መርኔ በጥሩ ቅልጥፍና ያገደበት አደገኛው ሙከራ ቀዳሚ ሊያደርጋቸው የቀረበ ነበር።

ጨዋታው 18ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ በተደጋጋሚ የተቃራኒ ቡድን ግብ ክልል ሲደርሱ የነበሩት ቡናማዎቹ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ አግኝተዋል፤ በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ አንተነህ ተፈራ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ከሳጥን ውጪ ለነበረው በፍቃዱ አለማየሁ ያቃበለውን ኳስ በፍቃዱ አለማየሁ አክርሮ መትቶ ግሩም ግብ መረብ ላይ አሳርፎ ቡናማዎቹን መሪ አድርጓቸዋል።

የግቡ መቆጠር ያነቃቃቸው ብርቱካናማዎቹ የሚያገኙትን እድል በሙሉ ወደ ግብ ለመቀየር በሙሉ ሀይላቸው ወደፊት ሲሄዱ ያስተዋልን ቢሆንም ይሄ ነው ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ሁነኛ ሙከራ በአጋማሹ አላስመለከቱን። ይሁን እንጂ እንቅስቃሴያቸውም መጥፎ የሚበል አለነበረም። ቡናማዎቹም እንዲሁ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩም ተመልክተናል።

ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ እያስመለከተ ጨዋታው ቀጥሎ 38ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ቡናማዎቹ ሁለተኛ ግብ መረብ ላይ አሳርፈው መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ አድርገዋል። ዲቫይን ዋቹኩዋ ከሳጥን ውጪ ሆኖ ያሻማውን ኳስ አንተነህ ተፈራ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥሮ ዞሮ መትቶ ወደግብነት ቀይሮታል። አጋማሹም በቡናማዎቹ ሁለት ለባዶ መሪነት ተገባዶ ወደመልበሻ ክፍል ገብተዋል።

ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ሲመለስ ብርቱካናማዎቹ ጠንከር ብለው ለመመለስ የሁለት ተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ወደሜዳ ገብተዋል። በዚህም በተደጋጋሚ ወደፊት በመሄድ ሙከራዎችን ለማድረግ ቢጣጣሩም አደገኛ የሚባል ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው 66ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ሱራፌል ጌታቸው ከሳጥን ውጪ ሆኖ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ከግቡ ቋሚ ብረት ርቆ ያለፈበት ሙከራ ለብርቱካናማዎቹ ከግብ ጋር ወደጨዋታው መመለስ የሚችሉበትን ተስፋ ይዞላቸው ለመምጣት የቀረበ አጋጣሚ ነበር።

ይበልጥ ደቂቃው እየገፋ ስሄድ ብርቱካናማዎቹ በቁጥር በርከት ብለው ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል እየደረሱ የቡናማዎቹን ተከላካይ መስመር መፈተናቸውን አጠናክረው ቀጥለውበታል ፤ ሆኖም ግን አደገኛ የሚባል ሙከራ ማድረግ ግን ተስኗቸዋል።  ቡናማዎቹ በአንፃራዊነት የፊት መስመራቸውን በአንድ ተጫዋች ብቻ በማስቀረት ረጃጅም ኳሶችን ከሜዳቸው እያራቁ በመልሶ ማጥቃት መጫወትን ምርጫቸው አድርገዋል።

82ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው የብርቱካናማዎቹ ተጫዋች አቡበከር ወንድሙ ርቀት ላይ ሆኖ አክርሮ መትቶ ያደረገው ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ ይቅር እንጂ ተጠቃሽ ሙከራ ነበር። ጨዋታው ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሲያመራ ብርቱካናማዎች ተስፋ አንግቦ የነበረው እንቅስቃሴያቸው እየተቀዛቀዘ ሲመጣ ያስተዋልን ሲሆን ቡናማዎቹ በበኩላቸው የሚያገኙትን አጋጣሚዎች በቅብብል ደቂቃ የመግደል አይነት እንቅስቃሴ አስመልክተውናል።

መደበኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ ተጠናቆ ጭማሪ በታየው ላይ ብርቱካናማዎቹ አደገኛ ቦታ ላይ ቅጣት ምት አግኝተው ሐቢብ ከማል በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ የግቡ አግዳሚ ባይመልስባቸው ምናልባትም የማስተዛዘኝ ግብ ለማግኘት ያቀረባቸው አጋጥሚ ሆኖ ተመዝግቧል። በመጨረሻም በእንቅስቃሴ ረገድ ጥሩ የነበረው በሙከራዎች መታጀብ ያልቻለው ሁለተኛው አጋማሽ ተጠናቆ ለቡናማዎች በመጀመሪያው አጋማሽ ሁለት ግቦች ጋር ሶስት ነጥብ በማጎናፀፍ ጨዋታው ተጠናቋል።