ፈረሰኞቹ በቢኒያም ፍቅሩ ብቸኛ ግብ ምዓም አናብስትን ድል ማድረግ ችለዋል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ሲካሄዱ መቐለ 70 እንደርታን ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አገናኝቷል። መቐለ 70 እንደርታዎች በ ባህር ዳር ከተማ በሰፊ ጎል ልዩነት ሽንፈት ካስተናገዱበት አሰላለፍ ኢማኑኤል ሳባንን በ ዘረሰናይ ብርሃነ ብቻ በመቀየር ወደ ሜዳ ሲገቡ በተመሳሳይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወልዋሎ ዓ.ዩን ካሸነፉበት ጨዋታ ፉዓድ አብደላን በ አፈወርቅ ኃይሉ በመተካት ጨዋታቸውን ጀምረዋል። መቐለ 70 እንደርታዎች ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከሽንፈት እንደመመለሳቸውን አንፃር የዛሬውን ጨዋታ አሸንፈው ካሉበት የወራጅነት ራሳቸውን ነፃ ለማድረግ ይሄ ጨዋታ እጅግ አስፈላጊ ነው። በተመሳሳይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ይህንን ጨዋታ አሸንፈው ተከታታይ ድላቸውን በማስመዝገብ የደረጃ ለውጥ ለማድረግ አስፈላጊ ጨዋታ ነው።
የመጀመሪያዎቹን 15 ደቂቃዎች ሁለቱም ክለቦች ተመጣጣኝ በሆነ የኳስ እንቅስቃሴ ጨዋታቸውን ማድረግ የቻሉ ሲሆን ከተከላካዮች ከሚነሱ ረጃጅም የአየር ላይ ኳሶች የማጥቃት ሙከራቸውን ለማድረግ ሲሞክሩ ተስተውሏል።
15ኛው ደቂቃ ላይ መነሻውን ከቀኝ መስመር ያደረገው ኳስ ሙሉጌታ ወ/ጊዮርጊስ በረጅሙ ያሾለከውን ኳስ የጊዮርጊሱ ተከላካይ ለመቆጣጠር ሲሞክር በመንሸራተቱ ያንን ኳስ ያገኘው አሸናፊ ሐፍቱ ቢሞክረውም በግቡ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። ረዘም ያሉ ደቂቃዎችን ያለ ሙከራ ያስመለከተን ጨዋታ ብዙም ለተመልካች ሳቢ ያልነበረ የመጀመሪያ አጋማሽ የነበረ ሲሆን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ይሄ ነው የሚባል የጎል ሙከራ ሳያስመለክተን 0-0 በሆነ ውጤት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ብዙም የጨዋታ ለውጦችን ሳያደርጉ የተመለሱት ሁለቱ ቡድኖች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ወደ ግብ መድረስ የቻሉ ሲሆን መቐለ 70 እንደርታዎች ከቀኝ መስመር በሚነሱ ኳሶች የማጥቃት ዒላማቸውን ሲያደርጉ በተመሳሳይ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ረጃጅም የአየር ላይ ኳሶችን እንደ ሁነኛ የማጥቂያ መንገድ አድርገው ግብ ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች በመጠኑም ቢሆን በጨዋታ እና የጎል ዕድል በመፍጠሩ ረገድ የተሻሉ ነበሩ።
የተጫዋች ለውጦችን በማድረግ ራሳቸውን አሻሽለው የቀረቡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች የመጀመሪያ ግባቸውን ማስቆጠር ችለዋል። 63ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር በኩል ተቀይረው ወደ ሜዳ የገቡት ዳግማዊ አርዓያ እና ሀብታሙ ጉልላት በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን በመግባት ያገኘውን ኳስ ሀብታሙ ጉልላት ወደ ጎል ቢመታውም ግብጠባቂው ሶፎንያስ መልሶበታል ነገር ግን ያንን የተመለሰውን ኳስ ያገኘው ቢኒያም ፍቅሩ ወደ ግብነት ቀይሮ ፈረሰኞቹን መሪ ማድረግ ችሏል።
ከግቡ መቆጠር በኋላ የአቻነት ግብ ለማግኘት ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት መቐለ 70 እንደርታዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በኳስ ብልጫ በመውሰድ በብዛት መድረስ የቻሉ ሲሆን 82ኛው ደቂቃ ላይ ያሬድ ከበደ ከመስመር ያሻማውን ኳስ ያገኘው ያሬድ ብርሃኑ በግንባሩ ገጭቶ ቢሞክረውም ግብጠባቂው ባህሩ ነጋሽ ግብ ከመሆን ታድጎታል። መቐለ 70 እንደርታዎች ግብ ለማስቆጠር ጫና አድርገው መጫወት ቢችሉም የቅዱስ ጊዮርጊሶችን የመከላከል አጥር መናድ ተስኗቸው ጨዋታው በፈረሰኞቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።