ሦስት ነጥብ እና ሦስት ደረጃዎች የሚለያቸው የባለፈው የውድድር ዓመት የዋንጫ ተፋላሚዎቹ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መቻል የሚያደርጉት ጨዋታ ከፍ ያለ ትግል እንደሚደረግበት ይጠበቃል።
በሰላሣ አምስት ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በመጨረሻው ሳምንት በሀዋሳ ከተማ ከገጠማቸው ሽንፈት በማገገም ድል የሚየስመዘግቡ ከሆነ ሦስት ደረጃዎች በማሻሻል በ5ኛ ደረጃ ላይ የሚቀመጡበት ዕድል በእጃቸው ይገኛል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁለተኛው ዙር እጅግ ተሻሽለው ከቀረቡ ክለቦች የሚጠቀስ ሲሆን ከውድድር ዓመቱ አጋማሽ በኋላ በተካሄዱ ሰባት ጨዋታዎችም አራት ድል፣ አንድ አቻ እና ሁለት ሽንፈቶች አስተናግዷል። ድንቅ ፍልሚያ በታየበት የሀዋሳ ከተማው ጨዋታ ሁለት ለአንድ የተረታው ቡድኑ ከሦስት መርሐ-ግብሮች መልስ ሽንፈት ያስመዝግብ እንጂ ፈታኝ በነበረው ጨዋታ ያሳየው እንቅስቃሴው ግን ለክፉ የሚሰጥ አልነበረም። ሆኖም ቡድኑ በከዚህ ቀደም ደረጃ ጨዋታዎች ለመቆጣጠር አለመቻሉ እና ለሳምንታት የዘለቀው የአፈፃፀም ድክመቱ ግን በነገው ዕለት መቀረፍ የሚገባቸው ችግሮች ናቸው። በሀዋሳ ከተማ ሽንፈት ባስተናገደበት ጨዋታ ላይ በተጋጣሚ የግብ ክልል አመርቂ አፈፃፀም ያልነበረው ቡድኑ በነገው ዕለት በተከታታይ ሦስት መርሐ-ግብሮች ላይ መረቡን በማስከበር በጥሩ ወቅታዊ ብቃት የሚገኘውን የጦሩ የመከላከል አደረጃጀት ለማስከፈት በብዙ ረገድ ተሻሽሎ መቅረብ ይኖርበታል።
ሦስት ተከታታይ ድሎች በማስመዝገብ
በሰሞኑ በጥሩ ብቃት ላይ ከሚገኙ ቡድኖች ውስጥ የሚጠቀሱት መቻሎች ነጥባቸው ከ40 በላይ ከፍ በማድረግ በፉክክሩ ለመዝለቅ በነገው ጨዋታ ሙሉ ነጥብ ያስፈልጋቸዋል።
ባለፉት ሦስት መርሐ-ግብሮች ከውጤቱም ባሻገር በእንቅስቃሴ ረገድ ጥሩ መሻሻል አሳይቶ በመደዳ ድሎች የተቀዳጀው ጦሩ በተለይም ከድሉ በፊት በተካሄዱ ስድስት መርሐ-ግብሮች ውስጥ በአምስቱ ኳስና መረብ ማገናኘት ተስኖት የነበረው የማጥቃቱ ክፍሉ ግሩም መሻሻል ማስመዝገቡን ተከትሎ ቡድኑን ወደ ውጤት ጎዳና መልሶታል። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች አራት ግቦች በማስቆጠር የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን ያስመሰከረው ሽመልስ በቀለ ደግሞ በነገው ጨዋታ የሚጠበቅ ተጫዋች ነው። በቅርብ ሳምንታት ካሳየው ለውጥ አንፃር ከፍ ባለ ጉልበት ጨዋታውን የሚጀምር፤ በሙሉ ኃይል የሚያጠቃ መቻል ነገም የሚጠበቅ ሲሆን ተጋጣሚው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የመውሰድ ዝንባሌ ያለው ቡድን መሆኑ ግን መሀል ሜዳ ላይ የሚጠብቀው ፈተና ከባድ መሆኑ አይቀሪ ነው።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል አንበሉ ፈቱዲን ጀማል አሁንም በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ እንደሆነ እና ተከላካይ ካሌብ አማንኩዋሀ ወደ ልምምድ ቢመለስም የመጫወቱ ነገር በአሰልጣኙ የሚወሰን ይሆናል። የተቀረው የቡድኑ ስብስብ ለጨዋታው ዝግጁ ነው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ለ28 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን መቻል 10 ጨዋታ በማሸነፍ ቀዳሚ ነው። ባንክ 5 ጊዜ ሲያሸንፍ 13 ጊዜ አቻ ተለያይተዋል። መቻል 38 ሲያስቆጥር ባንክ 31 አስቆጥሯል።