የጣና ሞገዶቹ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 2ለ0 በማሸነፍ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ብለዋል።
ከድል የተመለሱት ባህር ዳሮች ባለፈው ከተጠቀሙት አሰላለፍ ምንም ዓይነት የተጫዋች ለውጥ ሳያደርጉ ለጨዋታው ሲቀርቡ በተመሳሳይ ኢትዮ ኤሌትሪኮች በተስተካካይ መርሐ-ግብር ካሸነፉበት ስብስባቸው ምንም ለውጥ ባለማድረግ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በላይ ታደሰ ባስጀመሩት ጨዋታ የመጀመርያዎቹ አስር ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩም ሆኖ ወደ ፊት በመሄድ ብልጫ ወስደው የነበሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በ12ኛው ደቂቃ ላይ አሸናፊ ጥሩነህ ኳስ በእጅ በመንካቱ ፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቶባቸዋል። ምቱንም ግርማ ዲሳሳ በተገቢው መንገድ ወደ ጎልነት ቀይሮት ባህር ዳር ከተማን መሪ አድርጓል።
ከመጀመርያው አስር ደቂቃዎች መቀዛቀዝ በኋላ ጎል አስቆጥረው ወደ ጨዋታው እንቅስቃሴ የገቡት የጣና ሞገዶቹ በፍፁም አለሙ አማካኝነት የጎል ዕድል ፈጥረው የነበረ ቢሆንም ግብ ጠባቂው ኢዲሪሱ መክኖባቸዋል። ወደ አቻነት ለመመለስ የሚያደርጉት ጥረት መልካም ቢሆንም የማጥቂያ መንገዳቸው ጥድፊያ ይበዛበት የነበረ በመሆኑ ግልፅ የሚባል የጎል ዕድሎችን በመፍጠር ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ተቸግረው ታይተዋል። ጨዋታው የጎል ሙከራ ከማየት ዕርቆ በሁለቱም በኩል ወጥነት የሌለው የማጥቃት እንቅስቃሴ እያስመለከተን አጋማሹ በባህር ዳር አንድ ለምንም መሪነት ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር አሰልጣኝ ደግያረጋል ይግዛው ፍፁም አለሙን እና አቤል ማሙሽን አስወጥተው በፍሬው ሰለሞን እና ጄሮም ፊሊፕ ቀይረው ያስገቡት ፈጣን ቅያሪ ስኬታማ ሆኖላቸው በ47ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ጄሮም ፈሊፕ በቀኝ መስመር ያገኘውን ኳስ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ በጥሩ ሁኔታ ያሻገረውን ቸርነት ጉግሳ በግንባር ገጭቶ በማስቆጠር የቡድኑ የጎል መጠን ወደ ሁለት ከፍ አድርጎታል።
በጎሉ ይበልጥ የተነቃቁት የጣና ሞገዶቹ ጨዋታውን ይበልጥ መቆጣጠር የሚያስችላቸውን ተጨማሪ ጎል ፍለጋ በተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ለመድረስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ቀጥሎ 65ኛው ደቂቃ ተስፈኛው አማካይ ሄኖክ ይበልጣል ከፍሬው ሰለሞን የተቀበለውን ኳስ ከሳጥን ውጭ በግራ እግሩ አክሮ የመታውን ግብጠባቂው ኢድሪሱ እንደምንም ወደ ውጭ አውጥቶበታል።
ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በሁለት ጎሎች መመራት ውስጥም ሆነው የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ጎሎችን ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም የባህር ዳሮች የመከላከል ጥንካሬ ተደምሮ ስኬታማ መሆን አልቻሉም። የመጨረሻ አስር ደቂቃዎች በከባድ ዝናብ ውስጥ ሆኖ በቀጠለው ጨዋታ በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል አሸናፊ ጥሩነት በባህር ዳር በኩል ቸርነት ጉግሳ ከፈጠሩት የጎል ዕድሎች በኋላ በጭማሪ ደቂቃ ፊሊፕ ጄሮም በአስደናቂ ሁኔታ ከሜዳው ግራ ክፍል ከሳጥን ውጭ የመታውን ኳስ ግብጠባቂው ኢድሪሱ ካወጣበት የምታስቆጭ አጋጣሚ በኋላ ጨዋታው 2-0 በባህር ዳር አሸናፊነት ተፈፅሟል።