ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሲዳማ ቡና ከ መቻል

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | ሲዳማ ቡና ከ መቻል

ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ተመሳሳይ ውጤት ያስመዘገቡ በሦስት ነጥቦች የሚበላለጡ እና በጥሩ ወቅታዊ ብቃት የሚገኙ ክለቦችን የሚያፋልመው ጨዋታ ጥሩ ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል።

ከተከታታይ ሦስት ድሎች በኋላ በመጨረሻው መርሐግብር ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቶ የወጣው በሰላሣ ስድስት ነጥቦች 9ኛ ደረጃ የተቀመጠው ሲዳማ ቡና ወደ ሰንጠረዡ ወገብ ለመጠጋት ድልን እያለመ ወደ ሜዳ ይገባል።

ሲዳማ ቡና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከደረሰበት ሽንፈት በኋላ በተከናወኑ አራት ጨዋታዎች እጅ ካለመስጠቱ ባለፈ ተከታታይ ድሎች ማስመዝገቡን ተከትሎ ከነበረበት የስጋት ቀጠና እንዲላቀቅ ሆኗል። ቡድኑ በተጠቀሱት ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው አስራ ሁለት ነጥብ አስሩን ማሳካቱ፤ ከዚ ቀደም ለስህተቶች ተጋላጭ የነበረው የመከላከል አደረጃጀቱ ጉልህ ስህተቶች እየቀነሰ መምጣቱና ባለፉት አራት ጨዋታዎች በሦስቱ መረቡን አስከብሮ አንድ ግብ ብቻ ማስተናገዱ እንዲሁም በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ ስምንት ጨዋታዎች አንድ ሽንፈት ብቻ መቅመሱም በብዙ ረገድ እንደተሻሻለ ለመናገር በቂ ነው።

ሆኖም ከሰንጠረዡ አካፋይ ከፍ ለማለት እና ከስጋት ቀጠናው ርቆ ትንፋሽ ለመውሰድ የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ብቸኛ አማራጩ ነው። ይህ እንዲሳካም የማጥቃት ክፍሉን ይበልጥ ማጠናከር እና ባለፉት አራት ጨዋታዎች መረቡን ላላስደፈረው የጦሩ የኋላ ክፍል የሚመጥን አቀራረብ ማበጀት ከአሰልጣኝ አዲሴ ካሳ ቡድን የሚጠበቅ ነው።

ሰላሣ ዘጠኝ ነጥቦች በመሰብሰብ ከነገው ተጋጣሚያቸው በሦስት ነጥቦች ልቀው 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት መቻሎች ወደ 4ኛ ደረጃነት ከፍ የሚሉበትን ዕድል ለማመቻቸት ሲዳማ ቡናን ይገጥማሉ።

ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች እንዲሁም ከዘጠኝ ድል አልባ ሳምንታት አገግመው ባለፉት አራት ጨዋታዎች ወደ ተቃናው መንገድ የመጡት መቻሎች ከኢትዮጵያ ንግድ ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ በኋላ ሙሉ ነጥብ ማግኘት የሚችሉ ከሆነ ወደ መሪዎቹ የሚጠጉበት ዕድል ስለሚያገኙ በነገው ዕለት ባለፉት መርሐግብሮች የነበራቸው የመከላከል ጥንካሬዎች ማስቀጠል እንዲሁም ጠንካራ ፉክክር በተደረገበት የመጨረሻ ጨዋታ ላይ በፊት መስመሩ ላይ የተስተዋለው መጠነኛ መቀዛቀዝ ማረም ይኖርባቸዋል። ቡድኑ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ሦስት ድሎች ያስመዘገበና በጥሩ የማሸነፍ መንፈስ ያለ ተጋጣሚ ከሚፋለምበት ጨዋታ በፊት በጥሩ የመከላከል ብቃት ላይ መገኘቱ ከጨዋታው አንዳች ነጥብ ይዞ እንዲወጣ ያግዘዋል። ሆኖም ሲዳማ ቡና በመጨረሻዎቹ አራት መርሐ-ግብሮች በአንድ አጋጣሚ ብቻ መረቡን ያስደፈረ መሆኑ ሲታይ ግን የሚጠብቀው ፈተና ቀላል እንዳማይሆን መገመት ይቻላል።

በእንቅስቃሴ ረገድ ጥሩ ፉክክር እንደሚያስመለክተን በሚጠበቀው ጨዋታ በየፊናቸው በተከታታይ አራት ጨዋታዎች አራት ወሳኝ ግቦች ያስቆጠሩት ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን እና ሽመልስ በቀለ ይጠበቃሉ።

ሲዳማ ቡናዎች ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ ሆነው የነገውን ጨዋታ የሚጠባበቁ ይሆናል። በመቻል በኩል ግን የቡድኑ አምበል ምንይሉ ወንድሙ በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ሙሉ ለሙሉ ውጪ ሲሆን ሽመልስ በቀለ በበኩሉ ከሰሞኑ መጠነኛ ጉዳት በማስተናገዱ በጨዋታው የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ እንደሆነና የመጨረሻው ውሳኔ በጨዋታው ሰዓት መቃረቢያ እንደሚተላለፍ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ሁለቱ የነገ ተጋጣሚዎች ከዚህ ቀደም 27 ጊዜ ሲገናኙ ሁለቱም በእኩሌታ 10 ጨዋታዎች ላይ ድል አድርገዋል፤ 7 ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። መቻል 28፣ ሲዳማ 24 ጎሎች አስቆጥረዋል።