ብርቱካናማዎቹ ከወራጅ ቀጠናው ለማምለጥ የጣና ሞገዶቹ ደግሞ መሪዎቹን እግር በእግር ለመከታተል የሚፋለሙበት ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ባለው የነጥብ አስፈላጊነት ብርቱ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይገመታል።
ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች እና አንድ የአቻ ውጤት በኋላ አርባምንጭ ከተማን በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው በሦስት ነጥብ ከፍ ማለት የቻሉት ድሬዳዋ ከተማዎች ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ እያደረጉት ያሉትን ጉዞ ለማሳለጥ ባህርዳር ከተማን ይገጥማሉ።
መጨረሻው ጨዋታ ባስመዘገቡት ወሳኝ ድል እንዲሁም የቅርብ ተፎካካሪዎቹ የቅርብ ሳምንታት ውጤት የብርቱካናማዎቹ ጫና በውስን መልኩ እንዲቀንስ አድርጎታል፤ ያም ቢሆን ቡድኑ ከነገው መርሐ-ግብር ሙሉ ነጥብ ማስመዝገብን በምንም ሊተካው የማይችል ዓላማው ነው። በድሬዳዋ ከተማ ያለመውረድ ትግል ውስጥ አሁን እንደ ቡድን እየታየበት ያለው ጠንካራ ጎን ከሜዳ እንቅስቃሴ ባሻገር የተነሳሽነት መንፈሱ ነው። በእንደዚህ ዓይነት ወቅቶች በዚህ መጠን የቡድን መንፈስ ከፍ ማለቱ በራሱ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ይረዳል። ከአዞዎቹ ጋር በተደረገው የመጨረሻ ጨዋታም ያለ በቂ የማጥቃት እንቅስቃሴ ድል እንዲያስመዘግቡ ያላቸው ተነሳሽነት ያገዛቸው ይመስላል። ነገም ከከባድ ተጋጣሚያቸው ጋር ሲገናኙ የሰሞኑ የማሸነፍ ፍላጎት እና ቁርጠኝነት አብሯቸው ሊኖር የሚገባ ነገር ቢሆንም የጣና ሞገዶቹ ባለፉት አስራ አንድ ጨዋታዎች አራት ግቦች ብቻ የተመዘገቡበት ጠንካራ የመከላከል ውቅር ያለው ቡድን ያለው እንደመሆኑ ብርቱካናማዎቹ ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ይዘው ለመውጣት ፈተናው ከባድ ያደርግባቸዋል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወታቸውም ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ መቅረብ ግድ ይለዋል።
በአርባ ስምንት ነጥቦች 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህርዳር ከተማዎች በዋንጫ ፉክክሩ እስከመጨረሻው ለመዝለቅ በነገው ዕለት ድል ማድረግ አስፈላጊያቸው ነው።
ከሦስት ተከታታይ ድሎች በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተው የወጡት የጣና ሞገዶቹ በተጠቀሱት መርሐ-ግብሮች አራት ነጥቦች መጣላቸውን ተከትሎ ከመሪው በአስራ ሁለት ነጥቦች ለመራቅ ቢገደዱም መሪው መድን ዛሬ በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት ማስተናገዱን ተከትሎ በዋንጫ ፉክክሩ መዝለቅ የሚችሉበትን ዕድል አግኝተዋል።
የነገው ጨዋታ ከመሪው ጋር ያላቸውን ልዩነት ወደ ዘጠኝ በ2ኛ ደረጃ ከተቀመጠው ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ወደ ሦስት በማጥበብ በዋንጫ ፉክክሩ ለመቆየት የሚያስችላቸውን ዕድል የሚሰጣቸው እንደመሆኑ ለጣና ሞገዶቹ ወሳኝ ነው። ቡድኑ በወሳኙ መርሐ-ግብር ሙሉ ነጥብ ይዞ ለመውጣትም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች የተስተዋሉበትን የግብ ማስቆጠር ውስንነት ማረም ግድ ይለዋል። የጣና ሞገዶቹ በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ አስራ አንድ ጨዋታዎች ላይ አራት ግቦችን ብቻ በማስተናገድ እንዲሁም በሰባቱ መረባቸውን በማስከበር የመከላከል ጥንካሬያቸውን ማስቀጠል ቢችሉም ስምስት ግቦች በማስቆጠር ሦስት ተከታታይ ድሎች ካገኙባቸው መርሐ-ግብሮች በኋላ በተካሄዱ ሁለት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት አልቻሉም። ይህንን ተከትሎ በነገው ዕለት የማጥቃት አጨዋወቱን ጥንካሬ መመለስ ከአሰልጣኝ ደግአረግ ቡድን የሚጠበቅ ነው። ተጋጣሚያቸው ባለፉት አምስት መርሐ-ግብሮች ስድስት ግቦች ያስተናገደ እንደመሆኑ ከባድ ፈተና ይገጥማቸዋል ተብሎ ባይገመትም ጨዋታው ለድሬዳዋ ከተማ ካለው ትርጉም አኳያ ሲታይ ግን ምናልባትም ያልተጠበቀ ፈተና ሊገጥማቸው የሚችልበት ዕድል አለ።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ያለው መሐመድኑር ናስር በጉዳት አላዛር ማረነ ደግሞ በቅጣት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ውጭ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 11 አጋጣሚዎች የተገናኙ ሲሆን 4 ጨዋታዎች በነጥብ መጋራት ሲፈፀሙ ባህር ዳር ከተማዎች በ6 ጨዋታዎች ባለድል ሲሆኑ በአንፃሩ ድሬዳዋ ከተማዎች ደግሞ 1 ጨዋታ ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን በጨዋታዎቹ ባህርዳሮች 20 እንዲሁም ድሬዎች ደግሞ 8 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል። (የተሰረዘው የ2012 ውድድር ዓመት አልተካተተም)