ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ከመመራት ተነስቶ ድሬዳዋ ከተማን 3ለ1 በማሸነፍ ወደታችኛው ሊግ እርከን በወረደበት ዘመን የአመቱን ሁለተኛ ድል ተቀዳጅቷል።
የጨዋታ ሳምንቱ የሁለተኛ ቀን ቀዳማዊው መርሐግብር አስቀድመው ከሊጉ መሰናበታቸውን ያረጋገጡትን ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲን ደረጃቸውን ከፍ ለማድረግ ወሳኝ ጨዋታቸውን ከሚያደርጉት ከድሬዳዋ ከተማዎች አገናኝቷል። ድሬዳዋ ከተማ ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ሲያሸንፉ ከተጠቀሙበት ቋሚ ስብስብ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ አህመድ ረሺድ በድልአዲስ ገብሬ እና አቤል አሰበን በመስዑድ መሐመድ ተክተዋ ቀርበዋል። ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ በበኩላቸው በ32ኛው ሳምንት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ተጋርተው ሲወጡ ይዘው ከገቡት መጀመሪያ አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል፤ ሳምሶን ተካ እና ሰለሞን ገመቹን አሳርፈው በምትካቸው ማጌ አለምን እና ናሆም ሀይለማርያምን ይዘው ገብተዋል።
ምንም እንኳን በደረጃ ሰንጠረዡ በወራጅ ቀጠናው ላይ ባይገኙም ከስጋቱ ብዙም ያልራቁት እና ደረጃቸውን ለማሻሻል ወሳኝ ጨዋታቸውን እያደረጉ የሚገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ቀዳሚ ለመሆኑ ብልጫ ወስደው ሲጫወቱ ተመልክተናል።በ6ኛው ደቂቃ ላይ ብርቱካናማዎቹ የቢጫ ለባሾቹ ተከላካይ የአብስራ ሙሉጌታ ስህተት መነሻነት የተገኘውን ኳስ አስራት ቱንጆ ይዞ ግብቶ ከግብ ጠባቂው ጋር ቢገናኝም ናትናኤል ኪዳኔ በጥሩ ቅልጥፍና መልሶባቸዋል፤ በድጋሚም ግብ ጠባቂው በሰራው ጥፋት የተገኘውን ኳስ አስራት ቱንጆ እራሱ ከሳጥን ውጪ ሆኖ ረጅም ኳስ ወደ ግብ ቢመታም ግብ ጠባቂው ጥፋቱን ራሱ አርሞ ኳሷን በቀላሉ የተቆጣጠረባቸው ሌላኛው ተጠቃሽ አጋጣሚ ነበር።
ከስህተቶቻቸው መማር የቻሉት ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲዎች አቀራረባቸውን ቀይረው በኳስ ቁጠጥርም ሆነ ወደ ፊት በመሄድ ሂደት ሻል ያለ እንቅስቃሴ አድርገዋል፤ በዚህም 9ኛው ደቂቃ ላይ አደገኛ ሙከራ አድርገዋል፤ በመስመር በኩል ኳስ እየገፋ ይዞ የገባው ማጌ አለም ከሳጥን ውጭ ሆኖ መሬት ለመሬት አክርሮ የመታው ኳስ ለትንሽ ከግቡ ቋሚ ብረት ርቆ አልፎባቸዋል። እንዲሁምበ16ኛው ደቂቃ ላይ ሌላኛውን አደገኛ አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፤ ናትናኤል ሰለሞን በረጅሙ የተጣለውን ኳስ በግሩም ንክኪ ተቆጣጥሮ ግብ ጠባቂውን አታሎ በማለፍ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ኳሱን ለመምታት ጥረት ሲያደርግ ተከላካዩ ኢስማኤል አብዱል ጋኒዩ በግሩም መከላከል ጥበብ ደርሶ አስጥሎታል።
ጨዋታው በጥሩ ፉክክር ቀጥሎ የመጀመሪያው አጋማሽ አካፋይ እስኪደርስ ድረስ ሁለቱም ቡድኖች ወደ ፊት በመልሶ ማጥቃት እየገቡ ቀዳሚ ለመሆን ጥረት ሲያደርጉ የተመለከትን ሲሆን ቢጫ ለባሾቹ በተደጋጋሚ እየገቡ የድሬዳዋ ከተማዎችን ተከላካዮች በመፈተን እንዲሁም በኳስ ቁጥጥር የተሻለ እንቅሰቃሴ እያደረ አጋማሹ ወደ መጠናቀቅ ሲቃረብ ቢጫ ለባሾቹ በ39ኛው ደቂቃ ላይ በሱልጣን በርሄ አማካኝነት አድርገዋል፤ በርቀት ላይ ሆኖ ያደረገው ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ ይቅር እንጂ ተጠቃሽ ጠንከር ያለ ሙከራ ነበር።
አጋማሹ ሊጠናቀቅ ደቂቃዎች ሲቀሩት ቢጫ ለባሾች ሌላ አስቆጪ አጋጣሚ ፈጥረዋል፤ በ43ኛው ደቂቃ ላይ ጋዲሳ ማብራቴ የቆመ ኳስ ከመሃል ሜዳ አከባቢ ወደ ግብ ያሻማውን ኳስ የብርቱካናማዎቹ ተከላካይ ድልአዲስ ገብሬ በግንባሩ ገጭቶ ለማራቅ ጥረት ሲያደርግ ኳሱ ናትናኤል ሰለሞን ጋር ደርሶ ወደ ግብ የመታው ኳስ የግቡ ቋሚ ብረት ባይመልስባቸው ቀዳሚ ሆነው ወደ መልበሻ ክፍል እንዲገቡ ለማድረግ የቀረበ አጋጣሚ ነበር። አጋማሹም በቢጫ ለባሾቹ ግብ ማግባት ሙከራ በላይነት ነገር ግን ግብ ሳይቆጠርበት ተገባዶ ወደ መልበሻ ክፍል ገብተዋል።
ጨዋታው በሁለተኛ አጋማሽ ሲቀጥል ወልዋሎዎች ልክ እንደመጀመሪያው አጋማሽ አቀራረብ ተመልሰው የድሬዎችን ተከላካይ መስመር ፈትነዋል፣ 49ኛው ደቂቃ ላይ ሚኬኤሌ ኪዳኔ በግራ መስመር በኩል በእራሱ ጥረት ኳስ ይዞ ወደ ሳጥን ውስጥ ገብቶ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ከቋም ብረት በኩለል አልፎባቸዋል። በፈጣን ሽግግር የገቡት ብርቱካናማዎቹ ባልተጠበቀ መልኩ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። 52ኛው ደቂቃ ላይ ቻርልስ ሙሴጌ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ሳጥይ ውስጥ በተከላካዮች መካከል ሆኖ ለነበረው ኳሱን አሻግሮለት ዘረዓይ ገብረስላሴ በቀላል ንክኪ ወደግብነት ቀይሮታል።
አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት ቶሎ ወደ ጨዋታው መመለስ የቻሉት ቢጫ ለባሾቹ አምስት ደቂቃ ብቻ ጠብቀው የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል፤ 56ኛው ደቂቃ ላይ ከመሃል ሜዳ አከባቢ በረጅሙ የተጣለውን ኳስ ዳዊት ገብሩ በፍጥነት ደርሶ ወደ ሳጥን አሻግሮ ሱልጣን በርሄ ጠንከር ያለ ኳስ ወደ ግብ መጥቶ ከመረብ ጋር አገናኝቶ አቻ አድርጓቸዋል።
ድሬዳዋ ከተማዎች መሪ ለመሆን ወደ ፊት እየሄዱ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት እያደረጉ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ደግሞ በመልሶ ማጥቃት ወደ ፊት በፈጣን ኳስ እየደረሱ ጨዋታው 67ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የድሬዳዋ ከተማው ተከላካይ ድልአዲስ ገብሬ በሁለቱም አጋማሾች በተመለከታቸው ሁለት ቢጫ ካርዶች በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። የተጫዋች ጉድለትን ተጠቀምው ግብ ለማስቆጠር ወደፊት እየሄዱ የነበሩት ቢጫ ለባሾቹ 71ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ መረብ ላይ አሳርፈዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም ኃይለማርያም ያለቀ ኳስ በተከላካዮች መካከል ጣጣውን የጨረሰ ኳስ ሰንጥቆለት ናትናኤል ሰለሞን በፍጥነት ደርሶ የኳሱን አቅጣጫ ቀይሮ ከመረብ ጋር አገናኝቶ መሪ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።
ከ67ኛው ደቂቃ ጀምሮ በጎዶሎ ተጫዋቾች ለመጫወት የተገደዱት ብርቱካናማዎቹ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር በቁጥር በርከት ብለው በመግባት ጫና ሲያሳድሩ የተመለከትን ቢሆንም የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው ወደ መገባደጃው ተቃርቧል። ቢጫ ለባሾች በአንፃራዊነት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በመልሶ ማጥቃት የተጋጣሚያቸውን ግብ ክልል እየጎበኙ ቆይተው መሪነታቸውን ያጠናከሩበትን ግብ አግኝተዋል። 88ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ስምዖን ማሩ ያለቀ ኳስ ሳጥን አከባቢ አግኝቶ ከተከላካይ መካከል አሻግሮለት ዳዊት ገብሩ ከመረብ ጋር አገናኝቶ 3ለ1 እንዲመሩ አድርጓቸዋል። ጭማሪ በታየው ላይም በመልሶ ማጥቃት የግብ ማግባት ሙከራዎችን ሁለቱም ቡድኖች ቢያደርጉም ጨዋታው ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግድ 3ለ1 በሆነ ውጤት ለወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ወደታችኛው ሊግ እርከን በወረዱበት አመት ሁለተኛ ድል በማጎናፀፍ ተቋጭቷል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ለሱፐር ስፖርት አስተያየት የሰጡት የድሬዳዋ ከተማ ምክትል አሰልጣኝ ተረፈ ሂርጳሳ ”መከላከል አከባቢ በነበረው የትኩረት ማጣት ችግር ጎሎች ተቆጥረውብናል ፤ አጠቃላይ ሂደቱ ትክክል አልነበረም መከላከል አከባቢ የነበረው። ያለንበት የደረጃ ሰንጠረዥ ምንም እንኳን አስቸጋሪ ቢሆንም ብዙ ትኩረታችን ወደ ላይ መጠጋት እንደምንችል ነው ሁልጊዜ” የሚል ሃሳብ ሰጥተዋል። አሰልጣኝ አታክልቲ በረሃ በበኩላቸው ”ጨዋታው ባቀደኩበት መንገድ ሄዶልኛል ፤ ልምምድ የምንሰራበት ሜዳ በጣሞ አስቸጋሪ ነው በትንሹ ሜዳ እየሰራን አጨራረሱንም ሌላ ነገር ለመስራት ይከብዳል ፤ በዛ የተነሳ አጨራረስ ላይ ተቸግረን ነበር” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።