ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታቸውን 2ለ2 በሆነ ውጤት በማጠናቀቅ የውድድር ዓመታቸውን በአቻ ውጤት ዘግተዋል።
ሁለቱም ቡድኖች ከቀናት በፊት ድል ሲቀናቸው ከተጠቀሙት ቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ቡናዎቹ ከሸገር ደርቢው የዘጠኝ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደግሞ ከወላይታ ድቻው ጨዋታ የአራት ተጫዋቾችን ለውጥ በማድረግ ወደ ሜዳ ገብተዋል።
የመቋጫ ሳምንቱ ላይ የሚገኘው የሊጉ መርሐግብር በመጀመሪያ ቀኑ የመጀመሪያ የሆነውን የኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ጨዋታ ቀዳሚ በማድረግ በተያዘለት 9 ሰዓት ጅምሩን አድርጓል። የዕለቱ ዋና ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ በፊሽካቸው ያስጀመሩት ጨዋታ ጎል የተቆጠረበት በጊዜ ነበር ፣ በፈጣን ሽግግር ወደ መስመር ያደላውን እንቅስቃሴ ያደረጉት ንግድ ባንኮች 2ኛው ደቂቃ አዲስ ግደይ በረጅሙ የደረሰውን ኳስ ወደ ሳጥን በመጣል ሳይመን ከተቆጣጠራት በኋላ ሱለይማን ሀሚድ መልሶ ሲያሻማ ኪቲካ ጀማ በግንባር ገጭቶ ሀምራዊ ለባሾቹን መሪ አድርጓል።
ጎል በጊዜ ያስቆጥሩ እንጂ በተጋጣሚያቸው ኢትዮጵያ ቡና በብዙ ረገድ ለመበለጥ የተገደዱት ንግድ ባንኮች በድግግሞሽ በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ጥቃቶችን ለማስተናገድ ተገደዋል። ሀብታሙ አሸናፊ ከርቀት ባደረጋት እና ፍሬው ጌታሁን በመከታት አጋጣሚ ወደ ፊት በጥልቀት በመንቀሳቀስ ጥቃቶችን የጀመሩት ቡናማዎቹ በ11ኛው ደቂቃ ወደ ግራ ወደ ውስጥ እስራኤል ያቀበለውን ሀብታሙ አሸናፊ መቶ ፍሬው ጌታሁን እንደምንም አድኖበታል። በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት ከማድረግ ውጪ በእንቅስቃሴ ወረድ እያለ የመጡት ንግድ ባንኮች ወልደአማኑኤል እና ስንታየሁ ካደረጉት ሙከራ በኋላ የአቻነት ጎል ተቆጥሮባቸዋል።
በተለይ ስንታየሁ ዋለጪ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መቶ ፍሬው ጌታሁን ከመከታት አጋጣሚ መልስ ሁለት ደቂቃዎች ብቻ እንደተቆጠሩ ኪሩቤል ደሳለኝ ከማዕዘን አሻምቶ ወልደአማኑኤል ጌቱ በግንባር ገጭቶ ከመረብ ኳሷን አዋህዷታል። የተጋጣሚያቸውን ፋታ የማይሰጥ ተደጋጋሚ ማጥቃቶችን መከላከል እየከበዳቸው መጓዛቸውን የቀጠሉት ንግድ ባንኮች ይባስ ብሎ ሱሌይማን ሀሚድ ከኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ ሲዲ ማታላ ጋር በፈጠረው ሰጣ ገባ ጸብ አጫሪ ድርጊት በመፈጸሙ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ከተሰናበተ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ከቅጣት ምት ፈጥነው የጀመሩትን ኳስ ሀብታሙ ወደ ውስጥ ሰጥቶ ሲዲ እና ሀብታሙ በተከታታይ በግብ ዘቡ ፍሬው እና በተከላካይ የተመለሰውን ኳስ እስራኤል ሸጎሌ ሁለተኛ ጎል አድርጓታል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲመለስ ተመጣጣኝ ፉክክርን ነገር ግን በጎዶሎ የተጫዋች ቁጥር ወደ ሜዳ የገቡት ንግድ ባንኮች በረጃጅም ኳሶች በተሻለ ለመንቀሳቀስ ጥረት ያደረጉት ነበር። ከመጀመሪያው አንፃር ብዙም ሳቢ ያልነበረው ሁለተኛው አጋማሽ በንግድ ባንክ በኩል 67ኛው ደቂቃ ኤፍሬም ከማዕዘን አሻምቶ ሳይመን ፒተር በግንባር ገጭቶ ከወጣችበት ሙከራ መልስ 76ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉት የነበረው ጥረት ፍሬ አፍርቶ የአቻነት ጎልን አስቆጥረዋል።
ኤፍሬም ታምራት ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ባሲሩ ዑመር በግንባር ጨርፎ ያቀበለውን ኳስ ዮሐንስ ኪዳኔ ወደ ጎልነት በመለወጥ ጨዋታውን 2ለ2 አድርጓል። ከመጨረሻዋ ጎል መቆጠር በኋላ እያደጉ የመጡ እንቅስቃሴዎችን በሁለቱም ቡድኖች በኩል ማስተዋል ብንችልም በሙከራዎች ብዙም ያልደመቀው አጋማሽ በአቻ ውጤት ከድምዳሜ ደርሷል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የንግድ ባንኩ አሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ በጨዋታው አጀማመራቸው ጥሩ እንደነበር ጠቅሰው የሱሌይማን በቀይ መውጣት በዕቅዳቸው እንዳይጓዙ እንዳደረጋቸው እና አጠቃላይ ደረጃቸው የሚፈለገው ባይሆንም በጉዳት ከመታመሳቸው አንጻር በቂ እንደሆነ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ በበኩላቸው ከወትሮው በተለየ መመራት ተነስተው ሁለት ጎል ማስቆጠራቸው ያልተለመደ እና ዛሬ ያዩት ጠንካራ ጎን እንደሆነ ሲናገሩ 2ኛ ደረጃ ይዘው ማጠናቀቃቸው ከጠበቁት በላይ እንደሆነ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።