ሪፖርት | ፈረሰኞቹ በጭማሪ ደቂቃ ግብ ከጦሩ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | ፈረሰኞቹ በጭማሪ ደቂቃ ግብ ከጦሩ ነጥብ ተጋርተዋል

ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መቻል 1ለ1 በሆነ ውጤት ነጥብ በመጋራት የውድድር ዓመቱን ጨርሰዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት በሸገር ደርቢ 2ለ0 ሽንፈት ካስተናገደበት ከመጀመሪያ ቋሚ አሰላለፍ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ያብስራ ጎሳዬ፣ አፈወርቅ ኃይሉ፣ ዳግማዊ አርአያ እና አማኑኤል ኤርቦ አሳርፈው በምትካቸው አብርሃም ጌታቸው፣ ፋአድ አብደላ፣ በረከት ወልዴን እና ፍፁም ጥላሁንን ይዘው ሲገቡ መቻሎች በበኩላቸው በ35ኛው ጨዋታ ሳምንት በኢትዮ ኤሌክትሪክ 1ለ0 ሽንፈት ሲያስተናግዱ ከተጠቀሙበት ቋሚ አሰላለፍ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ዳግም ወንድሙን በአስቻለው ታመነ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ከሽንፈት የተመለሱ ቡድኖችን ያገናኘው የጨዋታ ሳምንቱ ሁለተኛ መርሐግብር በባህሩ ተካ መጀመሪያ ፊሽካ ጅማሮውን ሲያደርግ የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ፈረሰኞቹ በፈጣን ሽግግር ግብ ለማስቆጠር ይጣሩ እንጂ ሳጥን ውስጥ ገብተው አደገኛ ሙከራ ሳያደርጉ የከረሙበት ሲሆን መቻሎች በበኩላቸው ኳስ መስርተው እየተጫወቱ በቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ችለዋል። የጨዋታው ጅማሮ ላይ ወደ ፊት በመሄድ ረገድ የተሻለ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ፈረሰኞቹ  ምንም እንኳን አደገኛ የሚባል ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ባያደርጉም አስቆጪ አጋጠሚዎችን መፍጠር ችለዋል። በ13ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት መሬት ለመሬት የተሻገረውን ኳስ አሸናፊ ጌታቸው ከሳጥን ውጪ ሆኖ ሲመታው ቢኒያም ፍቅሩ ሳይዘጋጅ እግሩ ስር ደርሶ መትቶ ኢላማውን ሳይጠብቅ ይቅር እንጂ ሳጥን ውስጥ ገብተው ያገኙት የተሻለ አጋጣሚ ነበር።

ዘግይተው ወደ ማጥቃት እንቅስቀሴ የገቡት መቻሎች አደገኛ ሙከራዎች አድርገዋል፤ በተለይም 20ኛው ደቂቃ ላይ ኮሊን ኮፊ እና አቤል ነጋሽ ባደረጉት አንድ ለአንድ ቅብብል ያለቀ ኳስ ብቻውን ለነበረው ሽመልስ በቀለ አሻግሮለት በቀላሉ ወደ ግብነት ቀየረ ተብሎ ሲጠበቅ ኳሱን ከፍ አድርጎ ያመከነበት አስቆጪው አጋጣሚ ሲጠቀስ በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ዳግም አደገኛ ሙከራ በዮሴፍ ታረቀኝ አማካኝነት አድርገዋል፤ ሽመልስ በቀለ በተከላካዮች መካከል ያሻገረለትን ኳስ ዮሴፍ ታረቀኝ ከሁለት ተጫዋቾች መሃል ኳስ አግኝቶ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ የመታውን ኳስ ባህሩ ነጋሽ በጥሩ ቅልጥፍና ባይመልስባቸው መሪ ለመሆን የቀረቡበት ሌላኛው አደገኛው ሙከራ አይዘነጋም። ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶም ግብ አስቆጥረዋል፤ 30ኛው ደቂቃ ላይ መቻሎች በረጅሙ በተጣለ ኳስ ወደ ሳጥን በሚገቡበት ቅፅበት ባህሩ ነጋሽ ሽመልስ በቀለ ላይ በፈፀመው ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት ሲያግኙ አስቻለው ታመነ ወደ ግብነት ቀይሮ መሪ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

እንደአጀማመራቸው መሆን ያቃታቸው ፈረሰኞቹ አልፎ አልፎ ወደ ሶስተኛው ሜዳ ክፍል በሚጣሉ ኳሶች አቻ ሊያደርጋቸው የሚችል ግብ ፍለጋ ጥረት ያድርጉ እንጂ በተጋጣሚያቸው ሜዳ ክፍል ላይ ሲደርሱ ኳሶች እየተቆራረጠባቸው ተቸግረው ግልፅ የግብ ማግባት እድል መፍጠር ተስኗቸው አጋማሹ ወደ መገባደጃ ተቃርቧል። ጦሩ በአንፃራዊነት መሪ የሆኑበት ግብ በማስቆጠራቸው የኳስ ቅብብል በላይነት ወስደው ወደ ራሳቸው ግብ ክልል ኳስ እየመለሱ በእርጋታ ተቆጣጥረው ሲጫወቱ እያስተዋልን አጋማሹ ተገባዷል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ለመልሶ ፈረሰኞቹ የተጫዋች ቅያሪ አድርገው በፈጣን ማጥቃት አደገኛ ሙከራ ቢያደርጉም ግብ ጠባቂው ምንታምር መለሰ ሲመልስባቸው ግብ ለማስቆጠር የሚያደርጉትጰእንቅስቃሴ ጥረት ካላቸው ሙከራዎች ጋር መታጀብ ሳይችል ቀርቷል። ጦሩ በኳስ ቁጥጥርም ሆነ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ወደ ሳጥን እየደረሱ አደጋዎችን ሲፈጥሩ እየተመለከትን ጨዋታው ወደ ስልሳዎቹ ደቂቃዎች ገብቷል። ጨዋታው ዘለግ ላለ ደቂቃ ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ሳያስመለክተን ሰንብቶ 65ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ፈረሰኞቹ ወደ ጨዋታው እንዲመለሱ ያነቃቃቸውን ሙከራ አድርገዋል፤ ሀብታሙ ጉልላት ሳጥን ውስጥ ለነበረው አማኑኤል ኤርቦ ኳስ አሻግሮለት ጠጠር ያለ ኳስ መትቶ የግቡ ቋሚ ብረት መልሶበታል።

የፈረሰኞቹ ጫና በበረታበት በመጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች በተለይም ተቀይሮ በገባው በፀጋ ከድር አማካኝነት በቀኝ መስመር እየገቡ የመቻሎችን ተከላካይ መስመር ሲፈትኑ አስተውለናል። 73ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋ ከድር በመስመር በኩል ይዞ ገብቶ ለበረከት ወልዴ አሻግሮለት ደካማ ኳስ መትቶ ያመከነው አጋጣሚ ይታወሳል። በአጋማሹ የኋላ ኋላ ወደ አፈግፍገው የተቃራኒ ቡድን ጫና ማቋቋም ላይ ትኩረት ያደረጉት መቻሎች በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር አልፈው አልፈው ጥረት ያድርጉ እንጂ አብዛኛውን የጨዋታ ክፍለጊዜ በወገብ ወረድ ብለው ሲጫወቱ ለመመልከት ችለናል። እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ማጥቃቱን የቀጠሉት ፈረሰኞቹ ጭማሪ ደቂቃዎችም ላይ ፍፁም ለግብ የቀረቡ እድሎችን ፈጥረው ሳይጠቀሙ ሲቀሩ ያስተዋልን ሲሆን 94ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ወልዴ ከሳጥን ውጭ ሆኖ ያደረገው አደገኛው ሙከራ ግብ ጠባቂው ያገደባቸው የመጨረሻው አደገኛ ሙከራ ይታወስ እንጂ ጨዋታው በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠረ አስቻለው ታመነ ፍፁም ቅጣት ምት ብቸኛ ግብ ለጦሩ ሙሉ ሶስት ነጥብ በማጎናፀፍ ተጠናቀቀ ተብሎ የእለቱ ዋና ዳኛ ፊሽካ ሲጠበቅ ፈረሰኞቹ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። 90+10ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻማውን ኳስ ፍፁም ጥላሁን በግንባሩ ገጭቶ ኳስና መሰብ አገናኝቶ ጨዋታው 1ለ1 እንዲጠናቀቅ አድርጓል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የመቻሉ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ተደጋጋሚ ኳሶችን መሳታቸው ነጥብ ለመጣላቸው ምክንያት እንደሆኑ አንስተው ችግሮች ቢኖሩም ባላቸው ነገር ከዚህ የተሻለ ደረጃ ላይ መድረስ እንደነበረባቸው ተናግረዋል። የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በሰጡት አስተያየት በሁለተኛ አጋማሽ እንደነበራቸው ብልጫ ጎል ማግባታቸው እንደዘገየና ቀድሞ ማግባት እንደነበረባቸው ገልፀው በመጨረሻው ሰዓት በመጨረሻው ቀን ደጋፊዎች በመጨረሻ ደቂቃ ጎል ደስ ብሏቸው ሲወጡ ስላዩ ደስ እንዳላቸውና አንድ ነጥብ ማግኘታቸው የከፋ እንዳልሆነ ተናግረዋል።