ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | ኢትዮ ኤሌክትሪክ አራት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል

ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | ኢትዮ ኤሌክትሪክ አራት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል

አዲስ ሥራ አስኪያጅ እና አዲስ አሰልጣኝ የቀጠረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ አራት ተጫዋቾችን ለማስፈረም ተስማምቷል።

ከአራት የውድድር ዘመናት በኋላ ከአሰልጣኝ መሠረት ማኔ ጋር በመለያየት የቀድሞው ረዳት አሰልጣኙ ኤርሚያስ ዱባለን በዋና አሰልጣኝነት የቀጠሩት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በዛሬው ዕለት ከአራት ተጫዋቾች ጋር ሲያደርጉ የነበሩትን ድርድር በማገባደድ የስብስባቸው አካል ስለማድረጋቸው ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ግብ ጠባቂያዋ ንግስቲ መዓዛ ወደ ኤሌክትሪክ ያመራችዋ ቀዳሚዋ ፈራሚ ሆናለች። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ በግብ ጠባቂነት ያሳለፈችው የግብ ዘቧ ከረጅም ዓመታት በኋላ ወደ አዲስ ክለብ ስታመራ በሲዳማ ቡና ጥሩ የውድድር ዓመትን ያሳለፈችው የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዲስ አበባ ከተማዋ አጥቂ ዳግማዊት ሠለሞን ፣ በደደቢት ፣ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መቻል የተጫወተችው አማካዩዋ ትዕግሥት ያደታ ወደ ቀድሞው ክለቧ በድጋሚ ስትመለስ የቀድሞዋ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ልደታ ክፍለከተማ አማካይ ገብርኤላ አበበ የቀደመው አሰልጣኟን ተከትላ አዲሷ ፈራሚ ሆናለች።

ከክለቡ ጋር በተያያዘ ሥራ አስኪያጁ ሲሳይ ለማን ከቦታው በማንሳት በምትኩ ከደቡብ ሪጅን (ሀዋሳ ማዕከል) ጋዲሳ ለማን አዲሱ ሥራ አስኪያጅ አድርጎ ክለቡ ሾሟል።