የባላገሩ ቴሌቪዥን የስፖርት ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ አብይ ዘላለም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች የህዝብ ግንኙነት ባለሙያዎችን አለመያዛቸው መነሻ በማድረግ ተከታዩን ምልከታ አጋርተውናል።
በጋዜጠኛ አብይ ዘላለም
ኑሮውን በሰሜን አሜሪካ ሚኒሶታ ያደረገው የቀድሞ የቴዲ አፍሮ ማናጀርና የቅዱስ ጊዮርጊስ ህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ዘካሪያስ ጌታቸው (ዛክ) :- የህዝብ ግንኙነት ስራን ”የተቋም ደም ስር” ሲል ይገልፀዋል።
በተደጋጋሚ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ መረጃ ለማግኘት ጋዜጠኞች ስንቸገር በተገኘው አጋጣሚ የክለብ አመራሮቹን ”እኛም እናንተን እየደወልን ከምናጨናንቅ ዘመናዊ የኮሚኒኬሽን ባለሙያ ያስፈልጋችዋል ባለሙያ ቅጠሩ እያልን ለመጠቆም እንሞክራለን ።
ለዚህ ፁሁፍ ዝግጅት መረጃ ስሰበስብ ይፋዊ የህዝብ ግንኙነት  ባለሙያ ከኢትዮጵያ ቡናና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ውጪ በዚህ ዘርፍ የሚታወቅ ባለሙያ የለሞ (አሁን የሁለቱም ክለቦች ሙያተኞች በሰሜን አሜሪካ ኑሮአቸውን በማድረጋቸው የስራ ቦታው ክፍት ነው ) ሁለቱም ክለቦች ለስራ ቦታው ባለሙያ እንደሚቀጥሩም ተናግረዋል።

የሚዲያ ኦፊሰር በሚል ፎቶ የሚያነሱ ፣ግራፊክስ የሚሰሩ ፣ማህበራዊ ሚዲያውን ቁጥጥር የሚያደርጉ ባለሙያዎችን ብቻ በየክለቡ ታገኛላችሁ ። ህዝብ ግንኙነቱስ ?
ሶሻል ሚዲያ ማናጀር በሚባለው የስራ ዘርፍ ውስጥም ጥራት ትልቁ ጥያቄ የሚነሳበት እንደሆነ መታዘብ እንችላለን ።ለምሳሌ ይፋዊ የሜታ ባጅ ባለመኖሩ ምክኒያት ሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ በስሙ የተከፈተው ሀሰተኛ የሜታ ገፅ ከ100ሺ በላይ ተከታዮችን አፍርቷል ። ባህርዳር ከተማ እግር ኳስ ክለብ በቅርብ ጊዜ የክረምቱ የዝውውር መስኮት ላይ ያደረጋቸው አበረታች የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም እና በፕሮዳክሽን ውጤቶቹ ስሙ በጥሩ ሲነሳ እንደነበር ሲታወስ በዘርፉ ትልቅ ስራ እንደሚጠበቅ የሚያረጋግጥ ነው።
በህዝብ ግንኙነት ስራ ጥሩ ምሳሌ ሆኖ የሚታወሰው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደሆነ መታዘብ እንችላለን። ጎልተው ከወጡት የክለቡ ባለሙያዎች የማርኬቲንግ እና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ዘካሪያስ (ዛክ)እና አቶ አርሚያስ አሽኔን መጥቀስ እንችላለን። በተለይ በሁለቱ ባለሙያዎች ዘመን ከፍተኛ የኮሚኒኬሽን ስራ ለሰፊው የስፖርት ተመልካች መረጃዎችን በማድረስ የሰሩበት ዘመን ነበር ብሎ መመስከር ይቻላል ።
ለፈረሰኞቹ 3 አመታት ህዝብ ግንኙነት ስራ ላይ የነበረው የቀድሞ የቴዲ አፍሮ ማናጀር ዛክ ስለጉዳዩ አሳሳቢነት ያነሳውለትን ጥያቄ እንደሚጋራው በመናገር ይጀምራል:- ከሚዲያዎች፣ከጋዜጠኞች፣ ከስፖንሰሮች፣ከራስ ደጋፊዎች፣ከሌላ ክለብ ደጋፊዎች ባለን ግንኙነት በስራችን ፊት አውራሪ ነበርን እያለ ያስታወሳል። ይህም የኮሚኒኬሽን ባለሙያ የሚሰራው ትልቁ ጉዳይ እንደነበር ይናገራል።
ስር ነቀል ለውጥ መኖር አለበት ይላል ዛክ ።በዚህ ዘመን ክለቦች የኮምንኬሽን ዲፖርትመንት አለመኖሩ የሚያሳዝን ነው ህዝብ ግንኙነት ማለት የክለብ ደምስር ድልድይ ነው ሲል ጠቃሚነቱን ይገልፃል።
ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ክለብ ላይሰንሲግ ሀላፊው አቶ አምሀ ተስፋዬ:- አብዛኞቹ ክለቦች በቂ ግንዛቤ እንደሌላቸው በክለብ ላይሰንሲንግ ውስጥ የሙያ ቦታው አለ ግን የሰው ስም ሞልተው እንደሚመጡና እንደማይሰራበት አረጋግጠናል ይላል።በአሁኑ የውድድር ዘመን ባለሙያዎች ተመድበው እየሰሩ ስለመሆኑ እናጣራለን አስገዳጅ እንደሚሆንም ነው የነገረን ።
ጉዳዩ ትልቅ ነው …..
ኢትዮጵያ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚመረቁ በሺዎች የሚቆጠሩ ጋዜጠኝነት እና ኮሚኒኬሽን ሙያን ያጠኑ ባለሙያዎች ያሉባት ሀገር ናት ። ክለቦች በመንግስት በጀት እየተንቀሳቀሱ ነው ። ተመጣጣኝ ደሞዝ ከፍሎ ይህን የሰው ሀይል መጠቀም እንደ ሀገር ትልቅ ስራ መሆን ይችላል የስራ እድልም ከመፍጠር አንፃር።
የኢትዮጵያ ክለቦች በህዝብ ግንኙነት ዲፖርትመንት ውስጥ ብቁ ሚዲያ ማናጀር ባለመኖሩ ምክኒያት ኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ዲቻ የካፍ ክለቦች ውድድር ላይ ይህን ስራ የሰሩት የማይመለከታቸው የክለቡ ሰዎች መሆኑን ታዝበናል ።ክለቦቹ ኢትዮጵያን በአፍሪካ መድረክ እየወከሉ በአለም አቀፍ ግንኙነት ብቁ የሆኑ ባለሚያዎች ባለመኖራቸው በቦታው የሚፈጠሩ ትልልቅ የኮምኒኬሽን ስራዎች ዋጋ እንደሚያስከፍሉ ስለመረዳታቸው ያጠራጥራል።
የመፍትሄ ጥቆማዎች…
ክለቦች ዘመናዊ አደረጀጀት መከተል አለባቸው ተብሎ ከበርካታ  ጥናት በኋላ የሚቀርቡ ምክረ ሀሳቦች አሉ ። በቅርብ አመታት መዋዕለ ንዋይ እያፈሰሱ በሰው ሀይል እየተደራጁ ነው። በሌላው አለም ደግሞ ወደ ግዙፍ ተቋምነት ተቀይረዋል።  ኢንዱስትሪ እስከመሆን ደርሰዋል ። የሰው ሀይል አደረጃጀት ደግሞ ትልቁ መነሻቸው ነው  ።ለሀገር አጠቃላይ እድገት(GDP)  ቀጥተኛ ተፅእኖ መፍጠር እንደሚችል ጣሊያን፣ስፔን፣እንግሊዝ ምስክሮች ሲሆኑ ከአፍሪካ ታንዛኒያ ፣ሞሮኮ፣ ደቡብ አፍሪካና ናይጄሪያን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል  ይህም ዘመናዊ የክለብ አደረጃጀት ለመተግበር ከመሞከር የሚነሳ በቀጥታ የሚገናኝ ሀሳብ ነው። ዘመናዊ ክለቦች ሲኖሩ ተፅእኖዎቻቸው  የሀገር የሶሺዎ ኢኮኖሚ ውስጥም መጉላቱ አይቀርም።

ዘመናዊ አደረጃጀት ያላቸው ክለቦች የዘርፉ ባለሙያዎችን በጥቅል በ3 ዘርፍ ይከፍሉታል የማኔጅመንት ፣የፉትቦል እና ማች ዴይ በማለት ። በውስጡ ዝርዝር የሙያ ምደባዎች ይካተቱበታል ።የተወሰኑ አጥኚዎች  7 ዲፖርትመንት ፈጥረውለት  ክለቦች እንዲጠቀሙበት ይመክራሉ። በሁሉም ምክረ ሀሳቦች ግን ማረጋገጥ የቻልነው  በትኩረት ተጠቅሶ የምናገኘው ጉዳይ አሁን እየተወያየንበት ያለነው የሚዲያ ህዝብ ግንኙነት ክፍል ነዉ።
አቶ ዘካሪያስ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት በነበረበት ጊዜ የሚሰሩ ስራዎቹን በማስታወስ አሁን ክለቦች ምን ያህል እንደሚጎዱ ጠቅሶ መፍትሄው በእጃችን ነው ይላል ። ስር ነቀል ለውጥ ያስፈልጋል ።በቀላሉ በመረጃ በሚገኝበት ዘመን የእኛ ሀገር ክለቦች የኮሚኒኬሽን አሰራር መለወጥ እንደሚገባ ይመክራል። ዛሬ ጋዜጠኞች በቀላሉ የአውሮፖ ክለቦችን መረጃ እዚህ ኢትዮጵያ ሆነው አውሮፖ ካለው ጋዜጠኛ የበለጠ ቅርበት ኖሯቸው በሚያገኙበት ዘመን የኛው ክለቦች ለመረጃ አሰጣጥ የራቁ መሆናቸው ለእግር ኳሳችን እድገት ችግር እየፈጠሩ ስለመሆኑ እንዲታወቅ ያስፈልጋል ይላል ዛክ። ስለሆነም ብዙም ውስብስብ ነገር የሌለው በቀላል በጀት የሚሰራ እንደመሆኑ መጠን ክለቦች ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩበት ይመክራል ።
ማስታወሻ :- ክለቦች ይህን ዲፖርትመንት ትኩረት ሰጥተው ባለመስራታቸው ስለክለቦቹ ታሪክ ፣የተጨዋቾች ዳታ ፣ስታትስቲክና ሌሎች መረጃዎችን ዘመናዊ በሆነ መንገድ ለማግኘት ጋዜጠኞች በመቸገራቸው ኋላ ቀር የሆነ እና በመልካም ግንኙነት ላይ የተመሰረተ የተቆጠበ መረጃ ከአመራሩ ከተጨዋቾችና ከአሰልጣኞች ለማግኘት ሲጥሩ ይታያል።
በቀጣይ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ እየተሰሩ የሚገኙ የህዝብ ግንኙነት ስራዎች መልካም ጎኖች እና መሻሻል ስላለባቸው ጉዳዮች ተጨማሪ ፁሁፍ ይዤ እቀርባለሁ።
ስለፀሀፊው
ጋዜጠኛ አብይ ዘላለም ከባህር ዳር ዩኒቨርስቲ school of journalism በጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽንስ የመጀመሪያ ዲግሪውን ሰርቷል። በሚዲያ ውስጥ ከሪፖርተርነት እስከ ኤዲተርነት በብስራት ኤፍኤም፣በአሀዱ ቲቪ ፣ በአለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማህበር የሰራ ሲሆን አሁን በባላገሩ ቴሌቪዥን የባላገሩ ስፖርት ዋና አዘጋጅ ሆኖ እየሰራ ነው። በአሰልጣኝነት ሙያ የካፍ ዲ ላይሰንስ እና ከባርሴሎና ቶቮ አካዳሚ፣ከሆላንድ ፉትቦል ዩኒቨርስቲ አጫጭር ስልጠናዎችን ወስዷል።

