የወላይታ ድቻ የቦርድ አመራሮች የተለያዩ ውሳኔዎችን ማሳለፋቸውን የወላይታ ዞን መገናኛ ብዙሀኖች እየዘገቡ ይገኛሉ።።
ወላይታ ድቻዎች የ2018 ሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በአንደኛው ምድብ በሀዋሳ ከተማ በሚደረገው ውድድር ላይ ተደልድለው እስከ አራተኛ ሳምንት ድረስ ባደረጉት አራት ጨዋታ በሙሉ ሽንፈት በማስተናገድ በውጤት ማጣት ጉዞ ውስጥ እንደሚገኙ ይታወቃል።

ከዚህ ችግር ቡድኑ ይወጣ ዘንድ ትናንት ማምሻውን ስብሰባ የተቀመጠው የክለቡ ቦርድ ለውጤት ቀውሱ መፍትሔ ይሰጣል በማለት የተለያዩ ውሳኔዎችን እንዳሳለፈ የወላይታ ዞን መገናኛ ብዙሃን ማምሻውን መረጃዎችን በስፋት እያደረሱ ይገኛሉ።
በዚህም መነሻነት የቡድኑ ዋና አለቃ አሰልጣኙ ገብረክርስቶስ ቢራራ ከአሰልጣኝነታቸው እንዲነሱ እና ምክትል አሰልጣኙ ቴዎድሮስ ቀነኒ ቡድኑን በጊዛዊነት እንዲመሩ መደረጋቸው ሲሰማ በሌላ በኩል ክለቡን በስራ አስኪያጅነት ለረጅም ዓመታት (ሄድ መለስ እያሉ) ሲያገለግሉ የቆዮት አቶ አሰፋ ሆሲሶ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ በማድረግ በቦታው አቶ ምትኩ ኃይሌ እንደከዚህ ቀደሙ የአቶ አሰፋን ቦታ በውክልና እንዲሰሩ መሾማቸው ተሰምቷል።


