በ3ኛ ሳምንት ሊካሄድ ቀጠሮ ተይዞለት በመድን የኢንተርናሽናል ውድድር ምክንያት ዛሬ በተካሄደው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን ሸገር ከተማን በአማኑኤል ኤርቦ ብቸኛ ግብ 1-0 ማሸነፍ ችሏል።
በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ 3ኛ ሳምንት እንዲካሄድ መርሐግብር ወጥቶለት የነበረው እና ኢትዮጵያ መድን ከፒራሚድስ ጋር በነበረው የካፍ ቶታል ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ምክንያት የተራዘመው የሦስተኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐግብር ጨዋታ በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያ መድንን ከ ሸገር ከተማ አገናኝቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድን ይሄ ነው የሚባል የኳስ እንቅስቃሴ ያልታየበትና ለተመልካችም ያን ያህል ማራኪነት ያልነበረው ነበር። ኳስን ተቆጣጥሮ ወደ ፊት ተጠግቶ በመጫወት ረገድ ኢትዮጵያ መድን የተሻሉ የነበሩ ሲሆን 21ኛው ደቂቃ ላይ ወገኔ ገዛኝ ከሳጥን ውጪ ካደረገው ሙከራ ውጭ በሁለቱም ቡድን ይሄ ነው የሚባል ሙከራ ሳንመለከት የመጀመሪያው አጋማሽ ያለግብ ተጠናቋል።

ከዕረፍት መልስ ራሳቸውን አሻሽለው የቀረቡት ኢትዮጵያ መድኖች ብዙም ሳይቆይ የበላይነታቸውን ግብ በማስቆጠር አስመስክረዋል። በ48ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት አውላቸው ከሜዳው የቀኝ ክፍል ያሻማውን ኳስ አማኑኤል ኤርቦ በጥሩ አጨራረስ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ጫናዎችን በመፍጠር የአቻነት ግብ ለማግኘት ጥረቶችን ማድረግ የጀመሩት ሸገር ከተማዎች በ58ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር ከአንተነህ ተፈራ የተቀበለውን ኳስ ምስጋና ሚልኪያስ ወደ ግብ ቢመታውም ኳሱ ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታኮ ወደ ውጭ ወጥቶበታል።

በ80ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ መድኑ ረመዳን የሱፍ ከሳጥን ውጭ አክርሮ የመታው ኳስ በግብ ጠባቂው ባሕሩ ነጋሽ ጥረት ግብ ከመሆን ድኗል። የመደበኛው የጨዋታ ሰዓት መጠናቀቂያ 90ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ መድኑ ረመዳን የሱፍ ተቀይሮ በሚወጣበት ሰዓት ሆን ብለህ ጊዜ አባክነሃል በሚል ክስ የዕለቱ ዋና ዳኛ ሄኖክ አበበ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ አሰናብተውታል። ጨዋታውም በአማኑኤል ኤርቦ ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያ መድን ሸገር ከተማን 1-0 አሸንፈዋል።


