የሦስተኛ ዙር የኢትዮጵያ ዋንጫ ነገ በሚደረጉ አራት ጨዋታዎች ጅማሮውን ያደርጋል ፤ ጨዋታዎቹን አስመልክተን ያቀረብናቸውን መረጃዎች እነሆ !
መቻል ከ ድሬዳዋ ከተማ
በሁለተኛ ዙር የኢትዮጵያ ዋንጫ ሽረ ምድረገነትን እና ሀዋሳ ከተማን ረተው የመጡት መቻል እና ድሬዳዋ የሚያደርጉት የኢትዮጵያ ዋንጫ ተጠባቂ ጨዋታ 9፡30 ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል።
የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ውጤቶች የራቁት መቻል ባለፈው ዓመት በመለያ ምቶች ተሸንፎ የወጣበትን የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸንፎ ወደ አህጉራዊ የውድድር መድረክ መመለስ ዋነኛ ዓላማው ነው። በሁለተኛ ዙር ውድድር ሽረ ምድረገነትን በጥሩ ብቃት 3ለ0 ማሸነፍ የቻለው ቡድኑ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው የመጨረሻ 4 ተከታታይ ጨዋታዎች ጎል ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀት ላይ ትልቅ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል።
እንደ ተጋጣሚው ሁሉ ፕሪሚየር ሊጉ ወደ አዲስ አበባ ከመጣ በኋላ ድል ያላሳካው እና በሦስቱ አቻ ተለያይቶ በአንዱ የተሸነፈው ድሬዳዋ ከተማ ባለፉት አራት ጨዋታዎች አንድ ጎል ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት ኃይሉን ማነሳሳት የአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የነገ ዕቅድ እንደሚሆን ይገመታል።
ሁለቱ ቡድኖች ከ10 ቀናት በፊት በፕሪሚየር ሊጉ ተገናኝተው 1ለ1 መለያየታቸው ይታወሳል።
አቃቂ ቃሊቲ ከ ነጌሌ አርሲ
በሁለት የተለያየ የሊግ ደረጃ ላይ የሚገኙ ክለቦችን 04፡00 ሲል በሀዩስ የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያልፈውን ቡድን ይወስናል።
በሁለተኛው ዙር ሐረር ከተማን በቴዎድሮስ አበራ ሁለት ግቦች 2-1 በማሸነፍ ወደ ሦስተኛው ዙር የተሻገሩት አቃቂ ቃሊቲዎች ነገ በ4:00 ሰዓት ነጌሌ አርሲን ይገጥማሉ። አቃቂ ቃሊቲዎች የፕሪምየር ሊጉን ክለብ በመርታት በውድድሩ ለመቀጠል ከፍተኛ ትግል ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ነጌሌ አርሲ በመጀመርያው ዙር ሀዲያ ሆሳዕና ጋር በመደበኛው የጨዋታ ሰዓት አንድ እኩል (1-1) ከተለያዩ በኋላ በተሰጠ መለያ ምት ስምንት ለሰባት (8-7) በማሸነፍ ነበር ወደዚ የጨዋታ ዙር የተሸጋገሩት። ዘንድሮ በፕሪምየር ሊጉ ተሳታፊ የሆኑት ነጌሌ አርሲዎች በከፍተኛ ሊጉ ከሚገኘው አቃቂ ቃሊቲ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ቡድኑ የኢትዮጵያ ዋንጫ ተፋላሚ ለመሆን አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ይጥራል።

ባህር ዳር ከተማ ከ ቦዲቲ ከተማ
ሌላኛው የዕለቱ መርሐ ግብር ውስጥ አንዱ በሆነው ጨዋታ ባህር ዳር ከተማን ከ ቦዲቲ ከተማ 07፡00 ላይ በሀዩስ ያገናኛል።
በሁለተኛው ዙር ሸገር ከተማን በአማኑኤል ገ/ሚካኤል እና ግርማ ዲሳሳ ግቦች ታግዘው ሁለት ለባዶ (2-0) በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር የተሻገሩት ባህር ዳር ከተማዎች በፕሪሚየር ሊጉ አምና የነበረውን አቋም ዘንድሮ ማስቀጠል የተሳናቸው ሲሆን ቡድኑ የኢትዮጵያ ዋንጫን እንደ ማገገሚያ መድረክ በመጠቀም አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።
ቦዲቲ ከተማ በበኩሉ ሀላባ ከተማን በ አጥናፉ ቡሸና ሁለት ግቦች አማካኝነት ሁለት ለባዶ በማሸነፍ ነበር ወደዚህ ዙር የተሻገረው። የከፍተኛ ሊጉ ክለብ በፕሪምየር ሊጉ የብዙ አመታት ልምድ ካለው ባህር ዳር ከተማ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ትልቅ ፈተና እንደሚሆንበት ቢታወቅም፣ በዋንጫው ውድድር ድንገተኛ ውጤት ለማስመዝገብ ተስፋ አድርጎ ነገ ከቀኑ 7:00 ሰዓት ሲል ጨዋታውን ያደርጋል።
ኢትዮጵያ መድን ከ ቢሾፍቱ ከተማ
የሦስተኛው ዙር ሌላኛው ጨዋታ 9:30 ላይ በሀዩስ በኢትዮጵያ መድን እና በቢሾፍቱ ከተማ መካከል ይደረጋል።
በሁለተኛው ዙር ኢትዮ ኤሌክትሪክን በአማኑኤል ኤርቦ ብቸኛ ግብ አንድ ለባዶ በሆነ ውጤት በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር የተሻገሩት ኢትዮጵያ መድኖች በከፍተኛ ሊጉ የሚገኘውን ቢሾፍቱ ከተማን ይገጥማሉ። ኢትዮጵያ መድኖች በቅርብ ጊዜ በሊጉ ጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ባለመገኘታቸው፣ ከከፍተኛ ሊጉ ክለብ የሚገጥመው ፈተና ቀላል ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም። ይሁን እንጂ የፕሪምየር ሊግ ክለቡ በኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድር አሸናፊነትን በማስመዝገብ በሊጉ የገጠማቸውን አሉታዊ አቋም ለማስተካከል ይጥራሉ።
ቢሾፍቱ ከተማ በመጀመርያው ዙር ደሴ ከተማን በወንድማገኝ ዓለማየሁ ብቸኛ ግብ አንድ ለባዶ በማሸነፍ ነበር ወደ ሶስተኛው ዙር መሸጋገር የቻለው። በከፍተኛ ሊጉ ባደረጓቸው ስድስት ጨዋታዎች ውስጥ 5 ነጥብ በመሰብሰብ በምድብ ለ 6ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን ቡድኑ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ከሚያደርገው ጥረት በዘለለ፣ ከፕሪምየር ሊጉ ክለብ ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ያሉበትን የብቃት ደረጃ የሚለኩበት መሳሪያ አድርገው ይጠቀሙበታል።


