ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ እና ሀድያ ሆሳዕና ድል አድርገዋል

ሪፖርት | መቐለ 70 እንደርታ እና ሀድያ ሆሳዕና ድል አድርገዋል

ዛሬ በተጀመረው 11ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አዳማ ላይ በተደረጉ ጨዋታዎች ምዓም አናብስት እና ነብሮች ተጋጣሚያቸውን ማሸነፍ ችለዋል።

አርባ ምንጭ ከተማ ከ መቐለ 70 እንደርታ

ጨዋታው በሁለቱም ወገኖች በኩል መጠነኛ መቀዝቀዝ ቢታይበትም፣ የጨዋታውን ሂደት የቀየረችው ግብ በ14ኛው ደቂቃ ላይ ተቆጥራለች። መነሻውን ከቀኝ መስመር አድርጎ የተሻማውን ኳስ የአርባ ምንጩ ግብ ጠባቂ ጽዮን መርዕድ በአግባቡ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ ሲተፋው አጋጣሚውን በቅርብ ይከታተል የነበረው ብርሃኑ አዳሙ ኳሷን ወደ ግብነት በመቀየር የቀድሞ ክለቡ ላይ ግብ አስቆጥሮ ምዓም አናብስቶችን መሪ አድርጓል።

ግብ ካቆጠሩ በኋላ ይበልጥ ተጨማሪ ግብ ፍለጋ በተደጋጋሚ የተጋጣሚን የግብ ክልል መጎብኘት የቀጠሉት መቐለዎች  በ25ኛው ደቂቃ ላይ ከፍፁም አለሙ ጋር በጥሩ ከሳጥኑ ጋር አንድ ሁለት ቅብብል ወደ ሳጥን  የገባው ቦና ዓሊ ወደ ግብ ቢመታውም ኢላማውን መጠበቅ ተስኖት ወደ ውጭ ወጥቷል።

ከዕረፍት መልስ በቀጠለው ጨዋታ በ55ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም አለሙ ከሜዳው የቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ይዞት የገባውን እና ድንቅ በሚባል ሁኔታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ብርሃኑ አዳሙ ለራሱ እና ለክለቡ ሁለተኛውን ግብ በማስቆጠር ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። ሁለተኛ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ጨዋታውን በመቆጣጠር ግቦችን ለማስቆጠር ጥረት ያደረጉት አዞዎቹ በ81ኛው ደቂቃ ላይ ቡታቃ ሸመና በጥሩ ዕይታ ያቀበለውን ኳስ ተቀይሮ የገባው በፍቅር ግዛቸው ከግብ ጠባቂው ጋር ብቻውን ተገናኝቶ ከፍ አድርጎ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ወጥቷል ይህም ለአርባ ምንጮች ግብ ለማስቆጠር ወርቃማ ዕድል ነበር።

አልፎ አልፎ የቅጣት በትራቸውን መዘርጋት ያልተውት ምዓም አናብስቶች በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ በቦና ዓሊ እና ተቀይሮ በገባው አሸናፊ ሀብቱ አማካኝነት አስቆጪ ሙከራዎችን ያደረጉ ቢሆን ተጨማሪ ግቦችን ሳንመለከት ጨዋታው 2-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ወላይታ ድቻ

ምሽት 12:00 ላይ የተጀመረው ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና ከ ወላይታ ድቻ ጋር አግኝቷል። በኳስ ቁጥጥር እና ለእንቅስቃሴ ረገድ ተመጣጣኝ በነበረው ጨዋታው ቀድሞ ግብን በማስቆጠር ረገድ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ቀዳሚ ነበሩ። በ16ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ድቻ ተጫዋቾች የሜዳው የመሀል ክፍል ላይ በፈጠሩት መዘናጋት ተከትሎ ጫላ ተሽታ የነጠቀውን ኳስ እዮብ አለማየሁ ከግቡ ርቀት ሆኖ አክርሮ የመታው ኳስ ከመረብ ጋር ተገናኝቶ ሀዲያ ሆሳዕናን መሪ ማድረግ ችሏል።

ሀዲያ ሆሳዕናዎች ግብ ካስቆጠሩ በኋላም ጥቃታቸውን በመቀጠል መሪነታቸውን ወደ 2-0 ከፍ አድርገዋል። በ31ኛው ደቂቃ ላይ የወላይታ ድቻ ግብ ጠባቂ ቢኒያም ገነቱ ፀጋአብ ግዛው ላይ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ሄኖክ አርፌጮ ወደ ግብነት ቀይሮ የመጀመሪያው አጋማሽ በሀዲያ ሆሳዕና መሪነት እንዲጠናቀቅ አድርጓል።

ከዕረፍት መልስ ወላይታ ድቻዎች ራሳቸውን አሻሽለውና ከፍተኛ ጫና በመፍጠር ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት አድርገዋል። በዚሁ ጥረታቸው በ66ኛው ደቂቃ ላይ የሀዲያ ሆሳዕናው ተከላካይ ቃለአብ ውብሸት በራሱ የቅጣት ክልል ውስጥ ኳስ በእጅ በመንካቱ የዕለቱ ዋና ዳኛ ሚካኤል ጣዕመ የሰጡትን የፍጹም ቅጣት ምት መልካሙ ቦጋለ በልበ ሙሉነት ወደ ግብነት በመቀየር ለቡድኑ ተስፋን ሰጥቷል።

በተለይም በጨዋታው መገባደጃ ላይ የወላይታ ድቻ ተጫዋቾች ውጤቱን ለመቀልበስ ከፍተኛ ጫናዎችን ፈጥረው ሲጫወቱ የነበር ሲሆን በቴዎድሮስ ሀይለማሪያም የግንባር ኳስ ሙከራ ሲያደርጉ መከላከልን ምርጫቸው አድርገው በመልሶ ማጥቃት ተጨማሪ ግብ ለማግኘት  ጥረት የሚያደርጉት ነብሮቹ በተመስገን ብርሃኑ ከሳጥን ውጭ ከርቀት የሞከራት ኳስም ተጠቃሽ ነበረች።ይህንንም ተከትሎ ሀዲያ ሆሳዕናዎች 2-1 በሆነ ውጤት ወላይታ ድቻን አሸንፈዋል።