ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ13ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

ቅድመ ጨዋታ መረጃዎች | የ13ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

በሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይካሄዳሉ፤ መርሐግብሮቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እነሆ !

ነጌሌ አርሲ ከ መቻል

የዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ በአስገራሚ ግስጋሴ ላይ የሚገኘውን ነጌሌ አርሲ እና ከመሪዎቹ ተርታ እየራቀ የሚገኘውን መቻል ያገናኛል።

ሰገኖቹ በዘንድሮው የውድድር ዓመት ከከፍተኛ የሊጉ ወደ ፕሪሚየር ሊግ በማደግ ድንቅ የሚባል ግስጋሴን  እያስመለከቱን ሲሆን እስካሁን በሊጉ ባደረጓቸው በአሥራ ሁለት ጨዋታዎች አምስት ጊዜ ድል በማድረግ በአራቱ ነጥብ ተጋርተው፤ በሶስቱ ሽንፈት በማስተናገድ 19 ነጥቦችን በመሰብሰብ በደረጃ ሰንጠረዡ 6ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
የዛሬው ጨዋታም አስደናቂውን ጉዞ በማስቀጠል ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይቀርባሉ።

መቻሎች በበኩላቸው በዘንድሮው የውድድር ዓመት መልካም የሚባል ጅማሮ ማድረግ ቢችሉም አሁን ላይ ግን ያንን ጠንካራ አቋማቸውን ማስቀጠል ተስኗቸዋል። ቡድኑ በሊጉ ከተከታታይ ስድስት ጨዋታዎች በኋላ አዳማ ከተማን 3-1 በማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ቢመለስም ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈትን አስተናግዷል። ዳግም ወደ ድል መንገድ በመመለስ ከመሪዎቹ ተርታ ላለመራቅ የሚያደርጉት የዛሬው ጨዋታም ወሳኝነቱ ትልቅ ነው።

ነገሌ አርሲዎች በጉዳት ምክንያት ዘለግ ላሉ ሳምንታት ከሜዳ ከራቀው አብዱልበሲጥ ከማል በተጨማሪ በዛሬው ጨዋታ በረከት ወልዴ፣ ኢብሳ በፍቃዱ እና ገብረመስቀል ዱባለን በጉዳት አያሰልፉም። መቻል በ12ኛ የጨዋታ ሳምንት በጉዳት እና በብሔራዊ ቡድን ግዳጅ ምክንያት ውብሸት ጭላሎ፣ አማኑኤል ዮሐንስ፣ ኮሊንስ ኮፊ እና አሊዮንዚ ናፊያንን በዛሬው ጨዋታ አያገኝም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙ ይሆናል።

ሸገር ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ እና ወደ ወደ አሸናፊነት የተመለሰው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚያደርጉት ጨዋታ 09፡00 ሲል ይካሄዳል።

ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ተከታታይ ሽንፈትን ያስተናገዱት ሸገር ከተማዎች በሊጉ ወጥ የሆነ አቋም ማስመልከት ተስኗቸዋል። እስካሁን ባደረጓቸው ጨዋታዎችም በ6 ተሸንፈው በ12 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። በ12ኛው ሳምንት በመሪው ሲዳማ ቡና 2-0 የተሸነፈው ቡድኑ በዛሬው ጨዋታ ካለበት የሽንፈት ጎዳና ወጥቶ ወደ ድል ለመመለስ እና ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ብርቱ ፉክክር ማድረግ ይጠበቅበታል።

በተቃራኒው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካለፉት ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ ድል ቀንቶት በአንዱ አቻ በመውጣት በጥሩ ስነ-ልቦና ላይ ይገኛል። በሊጉ 15 ነጥቦችን በመሰብሰብ 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀምራዊ ለባሾቹ በመጨረሻው ሳምንት ከኢትዮጵያ መድን ጋር ባደረጉት ጨዋታ ላይ ከመመራት አንስራርተው 2-1 በማሸነፍ ጥሩ ሳምንት አሳልፈዋል። በዛሬው ጨዋታም ይህንን ተከታታይ ያለመሸነፍ ጉዞ ለማስቀጠል እና ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ ከፍ ለማለት ወደ ሜዳ ይገባሉ።

በሸገር ከተማ በኩል ሁሉም የቡድኑ አባላት በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኩል ደግሞ ቢንያም ካሳሁን በቅጣት ምክንያት አይሰለፍም፤ የካሌብ አማንክዋህ እና እንዳለ ዮሐንስ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ በሊጉ ታሪክ የመጀመሪያቸው ነው።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ምድረ ገነት ሽረ

ወደ ድል የተመለሱት ኢትዮጵያ ቡናዎች እና ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች ያስተናገዱት ሽረ ምድረ ገነቶች የሚያደርጉት ጨዋታ 10:00 ሲል ጅማሮውን ያደርጋል።

ከሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ መጣል በኋላ በመጨረሻው ሳምንት መቻልን 1 ለ 0 በማሸነፍ ወደ ድል የተመለሱት ኢትዮጵያ ቡናዎች 15 ነጥብ በመሰብሰብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ክለቡ አሰልጣኝ አብይ ካሳሁንን በማሰናበት በምትካቸው አሰልጣኝ ሳምሶን አየለን የቀጠረ ሲሆን አዲሱ አሰልጣኝም ቡድኑን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ የማድረግ ኃላፊነታቸውን ዛሬ የቀድሞ ክለባቸውን በሚገጥሙበት ጨዋታ ይጀምራሉ። በመጨረሻው ጨዋታ የታየው የድል ረሀብና የአሸናፊነት መንፈስ ማስቀጠልም ዋነኛው የአሰልጣኙ የቤት ስራ መሆኑ እሙን ነው።

በአንጻሩ ምድረ ገነት ሽረዎች ከድል ጋር ከተለያዩ እነሆ አራት ተከታታይ ጨዋታዎች አስቆጥረዋል። በ14 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቡድኑ ምንም እንኳን በደረጃ ሰንጠረዡ ከኢትዮጵያ ቡና በአንድ ዝቅ ብሎ ቢገኝም በሊጉ ጅማሮ ላይ ካስመዘገበው ውጤት እና ካሳየው እንቅስቃሴ አንፃር በብዙ ረገድ ተቀዛቅዟል።  በጨዋታ መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ በቡድኑ የሚታየው የትኩረት ማነስ እና የመከላከል ድክመቶችን ማረም ደግሞ የአሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ ዋነኛ የቤት ስራ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ በተከታታይ የተቀመጡ በመሆናቸው የዛሬው ጨዋታ አሸናፊ በደረጃው ላይ ከፍተኛ ለውጥ ለማምጣት የሚረዳው በመሆኑ ፍልሚያውን ጠንካራ ያደርገዋል።

በኢትዮጵያ ቡና በኩል ራምኬል ጀምስ ከቅጣት ሲመለስ ረጀብ ሚፍታህ በጉዳት ምክንያት አይኖርም። ሽረ ምድረ ገነቶች ግን በዛሬው ጨዋታ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ አራት ጊዜ የተገናኙት ሲሆን ቡናማዎቹ ሁለት ጊዜ ማሸነፍ ሲችሉ ምድረ ገነት ሽረዎች በቡላቸው አንድ ጊዜ ድል ሲያደርጉ በአንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርተዋል።በጨዋታዎቹም ቡና ሶስት ግቦች ሲያስቆጥሩ፤ ሽረዎች ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ ሲዳማ ቡና

በቅርብ ሳምንታት ተከታታይ ድሎች ካስመዘገቡ ቡድኖች የሚጠቀሱት  ነብሮቹ እና ሊጉን በመምራት ላይ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች የሚያደርጉት ጨዋታ በሳምንቱ ከሚከናወኑ መርሃ-ግብሮች ተጠባቂው ነው።

ሦስት ተከታታይ ድሎችን በማስመዝገብ በጥሩ የውጤታማነት ግስጋሴ ላይ የሚገኙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በ16 ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። የአሰልጣኝ ካሊድ መሐመድ ቡድን ከሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ በመከላከሉ እንዲሁም በማጥቃቱ ረገድ ያሳየው የሚታይ መሻሻልም ለሦስት ተከታታይ ድሎች አብቅቶታል። በቅርብ ሳምንታት የታየው ሁለንተናዊ ለውጥ የተመዘገቡት ውጤቶችም ዛሬ ከመሪው ጋር ለሚያደርጉት ጨዋታ ትልቅ በራስ መተማመን እንደሚሰጣቸውም ይጠበቃል።

በሌላ በኩል የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና በ25 ነጥቦች የደረጃ ሰንጠረዡን አናት ተቆጣጥሮ ይገኛል። ቡድኑ በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ነጥብ በመጋራት መሪነቱን ስጋት ላይ ወድቆ የነበረ ቢሆንም ባለፈው ሳምንት ሸገር ከተማን በማሸነፍ ዳግም ወደ አሸናፊነት ተመልሷል። በውድድር ዓመቱ  አንድ ሽንፈት ብቻ ያስተናገዱት ሲዳማ ቡናዎች ፋሲል ከነማ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ የነጥብ ልዩነቱን በማስፋት መሪነታቸውን ለማጠናከር ወርቃማ ዕድል አግኝተዋል። ሆኖም ሦስት ተከታታይ ድሎች አስመዝግቦ በጥሩ መነሳሳት ላይ ካለው ሀዲያ ሆሳዕና የሚጠብቃቸው  ፈተና ፈታኝ እንደሚሆን ይጠበቃል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 12 ጨዋታዎች አድርገዋል። አራት ጊዜ ነጥብ ሲጋሩ 20 ግቦች ያሉት ሀዲያ ሆሳዕና አምስት ፣ 13 ግቦች ያሉት ሲዳማ ቡናም ሦስት ድሎችን አስመዝግበዋል።