14ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዛሬም ቀጥሎ ሲካሄድ የዕለቱን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ
በ17 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች ወጥነት ከሌለው አካሄድ ተላቀው ደረጃቸውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ብርቱካናማዎቹ ካደረጓቸው 13 ጨዋታዎች አራት አራት ጊዜ ድልና ሽንፈት በእኩሌታ እንዲሁም አምስት የአቻ ውጤቶች አስመዝግበዋል። ከመጨረሻዎቹ ስምንት ጨዋታዎች ውስጥ በሁለት አጋጣሚ ብቻ ድል ያስመዘገበው ቡድኑ ዳግም ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት ያልቻለውን የፊት መስመሩ
ውጤታማነት በማሳደግ ረገድ ትልቅ የቤት ስራ ይጠብቃቸዋል።
በ21 ነጥቦች 6ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከመሪዎቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ዛሬ ጨዋታ ወሳኝ ያከናውናል። ኤሌክትሪክ በሊጉ ሁለት ሽንፈቶችን ብቻ ያስተናገደ ቡድን ነው፤ ቡድኑ በሊጉ አንድ ጨዋታ ብቻ ከተሸነፈው ሲዳማ ቡና ቀጥሎ ጥቂት ሽንፈት የቀመሰ ቡድን ቢሆንም እንደ ተጋጣሚው ሁሉ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ድል ማድረግ የቻለው በአንዱ ብቻ ነበር። በቅርብ ሳምንታት የሚታይበትን መቀዛቀዝ ለመቅረፍም በመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ብቻ ያስቆጠረውን የፊት መስመር ማሻሻል ይኖርባቸዋል።
ድሬዳዋ ከተማ በዛሬው ጨዋታ አስቻለው ታመነ፣ አቤል አሰበ፣ ጀሚል ያቆብ እና አብዱልሰላም የሱፍን በጉዳት ምክንያት የማይጠቀም ሲሆን ያሬድ ታደሰ እና አቡበከር ሻሚል ደግሞ የመሰለፋቸው ነገር በጉዳት ምክንያት አጠራጣሪ መሆኑ ተጠቁሟል። ባሳለፍነው ጨዋታ ያልተሰለፈው ተከላካዩ ሬድዋን ሸረፋ ግን ከቅጣት መልስ ለጨዋታው ዝግጁ እንደሆነ ተመላክቷል። በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል በጉዳት ላይ የሰነበቱትን አብዱላሂ አላዩ እና አብነት ተስፈዬ አሁንም በዛሬው ጨዋታ አንመለከታቸውም።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ18 ጊዜያት ተገናኝተው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ7፤ ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ በ4 አጋጣሚዎች ሲያሸንፉ ቀሪዎቹ 7 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ የተጠናቀቁ ነበሩ። ኤሌክትሪክ 22 ድሬዳዋ ደግሞ 14 ግቦችን ማስቆጠርም ችለዋል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
በሁለት ነጥብ ተበላልጠው በደረጃ ሰንጠረዡ አጋማሽ ላይ የተቀመጡትን ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ ከዕለቱ ተጠባቂ መርሃ ግብሮች መካከል አንዱ ነው።
ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻሉት ሀዋሳ ከተማዎች ካደረጓቸው 13 ጨዋታዎች 21 ነጥቦችን በመሰብሰብ በ5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። ሀይቆቹ በሊጉ 6 ድል፣ 4 ሽንፈት እና 3 የአቻ ውጤት በማስመዝገብ ምናልባትም በክለቡ ታሪክ ከታዩ መጥፎ አጀማመሮች አንዱ ከነበረው የባለፈው ዓመት ጅሟራቸው መላቀቅ ቢችሉም በቅርብ ሳምንታት ግን መጠነኛ መቀዛቀዝ ገጥሟቸዋል። በሦስት ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ካስቆጠረ በኋላ ቡድኑ ሽንፈት እና አቻ ባስመዘገበባቸው ያለፉትን ሁለት መርሐግብሮች ላይ ግብ ማስቆጠር ያልቻለውን የፊት መስመር ዳግም ማነቃቃት ደግሞ ከአሰልጣኙ ይጠበቃል።
በ13 ጨዋታ 19 ነጥብ ሰብስቦ 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ ዳግም ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ አናት ለመጠጋት የሚያግዘውን ድል ለማግኘት ወደ ጨዋታው ይቀርባል።
ፈረሰኞቹ በመጨረሻዎቹ አምስት ጨዋታዎች ድል ማድረግ አልቻሉም። ያለፉትን አራት ጨዋታዎች በተከታታይ የአቻ ውጤት ያስመዘገበው ቡድኑ ከሽንፈት መራቁ እንደ አወንታዊ የሚጠቀስለት ነጥብ ቢሆንም የሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ግን ወጥነት ይጎድለዋል። ፈረሰኞቹ ከሚታይባቸው ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት የማጠናቀቅ አባዜ ለመላቀቅም የሚስተዋሉባቸውን የመከላከል ድክመቶች ማሻሻል እንዲሁም ከአቤል ያለው መለለስ በኋለ መጠነኛ መሻሻል ያሳየውን የፊት መስመር ማጎልበት ግድ ይላቸዋል።
ሀዋሳ ከተማዎች በዛሬው ጨዋታ በጉዳትም ሆነ በቅጣት የሚያጡት ተጫዋች የለም። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩልም ከአጥቂው ቢንያም በላይ በስተቀር ሁሉም የቡድኑ አባላት ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች 51 ጊዜ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 29 ጊዜ ባለድል ሲሆኑ ሀዋሳ ከተማ 9 ጊዜ አሸንፈዋል። ቀሪዎቹ 13 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። ፈረሰኞቹ 87፣ ሐይቆቹ 40 ግቦች አስቆጥረዋል።
መቐለ 70 እንደርታ ከ ሸገር ከተማ
በታችኛው የደረጃ ሰንጠረዡ ክፍል በአንድ ነጥብ ብቻ ተበላልጠው 15ኛ እና 16ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት እና ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ብርቱ ትግል ማድረግ የሚጠበቅባቸው ቡድኖችን የሚያገናኘው ጨዋታ የሳምንቱ ሌላኛው ተጠባቂ መርሃ-ግብር ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አስደናቂ መነቃቃት እያሳዩ የሚገኙት ምዓም አናብስቶች ባደረጓቸው 13 ጨዋታዎች 12 ነጥቦችን በመሰብሰብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ቡድኑ የውድድር ዓመቱን በአስቸጋሪ ሁኔታ ቢጀምርም ባለፉት ሦስት ተከታታይ ጨዋታዎች ግን ሽንፈት አላስተናገደም። ካለፉት ሦስት መርሐ ግብሮች ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥብ ሰባቱን ማሳካቱ እንዲሁም የሜዳ ላይ እንቅስቃሴው በብዙ ረገድ መሻሻሉም ቡድኑ በጥሩ መነቃቃት እንዳለ ማሳያዎች ናቸው። ይህን ግስጋሴያቸውን አስቀጥለው ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣትም በቅርብ ሳምንታት በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ረገድ የታየባቸውን መሻሻል ማስቀጠል ግድ ይላቸዋል።
በ13 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ሸገር ከተማ ከወራጅ ቀጠናው አፋፍ ለመራቅ የሚያግዘውን ድል ለማግኘት ወደ ጨዋታው ይቀርባል። ሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች እና አንድ የአቻ ውጤት በማስመዝገብ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ድል ማድረግ ያልቻለው ቡድኑ ከገጠመው የውጤት ቀውስ ለመውጣት ዘርፈ ብዙ ለውጦች ማድረግ ይኖርበታል። በተለይም ባለፉት አራት ጨዋታዎች ስምንት ግቦች ማስተናገደ የቻለው የመከላከል አደረጃጀቱ አንገብጋቢ ለውጥ የሚሻ የቡድኑ ደካማ ጎን ነው።
መቐለ 70 እንደርታዎች በዛሬው ጨዋታ ጉዳት ላይ የሰነበቱትን ሱሌይማን ሐሚድ፣ ቦና ዓሊ፣ ዘርኢሰናይ ብርሀነ፣ አማኑኤል ልዑል እና ዮሐንስ ዓፈራ ግልጋሎት አያገኙም። በሸገር ከተማ በኩል መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
ሁለቱም ቡድኖች በሊጉ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙ ይሆናል።

