ሪፖርት | ሸገር ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | ሸገር ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል

ሸገር ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ያገናኘው የዕለቱ የአዲስ አበባ ስታድየም ብቸኛ ጨዋታ ግብ ሳይቆጠርበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል

ሸገር ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ
በመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ድሬዳዋ ከተማዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ የወሰዱበት ሸገር ከተማዎች ደግሞ ወደ ኋላ አፈግፍገው የተንቀሳቀሱበት ሲሆን በአጋማሹም ሁለቱም ቡድኖች በተመሳሳይ ውጤታማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ አልቻሉም። አንተነህ ተፈራ ከሳጥን ውጭ ያደረጋት እና በግቡ አግዳሚ በኩል ከወጣችው ዓላማዋን ያልጠበቀች ሙከራ ውጭም በአጋማሹ ይሄ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳይደረግ ቡድኖቹ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሸገር ከተማዎች ከተጋጣሚያቸው አንፃር የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉበት ነበር። ሆኖም አጋማሹ እንደ መጀመሪያው የጨዋታ ምዕራፍ ሁሉ በሙከራዎች ያልታጀበ ነበር። አጋማሹ በደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ይሄ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳይደረግበት እስከ 80ኛው ደቂቃ ከዘለቀ በኋላ አንተነህ ተፈራ አምበሉ ሄኖክ አዱኛ ከተከላካዮች ጀርባ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ መቷት ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን እንደ ምንም ግብ ከመሆን ያዳናት ሙከራም ሸገርን መሪ ለማድረግ የተቃረበች ሙከራ ነበረች።

በሁለቱም አጋማሾች ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ
የተደረገበት በሙከራዎች ያልታጀበ ጨዋታም 0-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።