ትኩረት | ዳኝነታችን ወደ የት እያመራ ነው?

ትኩረት | ዳኝነታችን ወደ የት እያመራ ነው?

ለመረዳት የሚያስቸግሩ ግራ አጋቢ የዳኝነት ውሳኔዎች ተበራክተዋል ፤ ስህተት ያለና የሚኖር ቢሆንም ቸልተኝነቱ ግን መላ ሊባል ይገባል!

የ2018 የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ወደ እኩሌታው እየተጠጋ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ከጨዋታዎች መጠናቀቅ በኃላ ቀዳሚው ርዕሰ ዜና የዳኝነት የውሳኔ ስህተት እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል ፤ ይባስ ብሎ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ፈፅሞ ግራ የሚያጋቡ ውሳኔዎችን የተመለከትንበት ሆኖ አልፏል። ለአብነትም ሀዲያ ሆሳዕና በወልዋል ዓ.ዩ በተሸነፈበት ጨዋታ ደስታ ዋሚሾ ለሀዲያዎች ያስቆጠሯት በግልፅ ከጨዋታ ውጭ የሆነች ግብ ፣ ቃልኪዳን ዘላለም ፋሲል ከነማ አርባምንጭ ከተማን ሲረታ በእጁ ያስቆጠራት ግብ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከምድረ ገነት ሽረ ያለግብ አቻ ሲለያይ በመጨረሻ ደቂቃ ፍፁም ጥላሁን በግንባሩ አስቆጥራት የተሻረችው ግብ በጨዋታ ሳምንቱ ትኩረት የሳቡ ክስተቶች ናቸው።

እነዚህ እንደው ጎልተው ስልወጡ አነሳን እንጅ በቀደሙት ሳምንታት ሌሎች ስፍር ቁጥር የሌላቸው የዳኝነት ግድፈቶችን ስንታዘብ ሰንብተናል ፤ ሌላው በሊጋችን የዳኝነት ስርዓት የሰርክ ግድፈት የሆነው በፈጠራ አቅማቸው የላቁ ተጫዋቾች እጥረት በሚታመሰው ሊጋችን ዳኞችን እነዚህን ተጫዋቾች ከመጠበቅ አንፃር እዚህ ግባ የሚባል ስራን ሰርተዋል ብለን ለመናገር በሚያስቸግር ሁኔታ ከሌሎች በተለየ ኳስ በእግራቸው ስር የሚያቆዩት እነዚሁ ተጫዋቾች ላይ የሚሰነዘሩ “ለግድያ ሙከራ” የቀረቡ ጥፋቶች በቸልታ ሲታለፉ መመልከት እየተለመደ መጥቷል።

እርግጥ ስህተት መቼም ቢሆን ስህተት መሆኑ እንዳለ ሆኖ ከሰሞኑ እጅግ እየተበራከቱ የመጡት የዳኝነት ስህተቶች በመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ሆኖ እንጂ አይበለው እና ሁሉም ጨዋታ እጅግ ውድ ዋጋ በሚኖረው ሁለተኛ ዙር ላይ ለምሳሌ በ30ኛ ሳምንት ጨዋታ ቢሆን ሊፈጠር የሚችለው ውዝግብ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን መገመት አያስቸግርም።

አዎ ዳኞች ሰዎች ናቸው ፤ እኛ ከክስተቶቹ በኃላ ደጋግመን የምናያቸውን ክስተቶች እነሱ በሚሆንበት ቅፅበት (real time) አንድ ጊዜ ተመልክተው ውሳኔ እንደመስጠታቸው ስህተቶች ሰዋዊ መሆናቸው ለመገንዘብ የተለየ መረዳት አይጠይቅም ነገርግን አንዳንዶቹ በተለይ ሰሞነኛ ስህተቶች ግን አይደለም በፕሪምየር ሊግ ከሚያጫውት ዳኛ ይቅር እና በሰፈር ውስጥ ያለ ረዳት ዳኛ በሚመሩ ጨዋታዎች ላይ ፈፅሞ ልንመለከታቸው የማንችላቸው ፍፁም የጎሉ የመሰረታዊ የጨዋታ ህግ አረዳድ ክፍተቶችን ታዝበናል።

ከቀናት በፊት በሀገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ETV ላይ ስለ ሀገሪቱ የእግር ኳስ ዳኝነት በተደረገ የቀጥታ ውይይት ወቅት የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ የሆነችው ኢንስትራክተር ሊዲያ ታፈሰ በዚህ ዓመት በሊጉ እየታዘቡ ያሉት ዳኝነት እጅግ የከፋ እንደሆነ የገለፀች ሲሆን አያይዛም “ዳኞች ስህተታቸውን እንዲያርሙና እንዲማሩበት የጨዋታ ቪዲዮዎችን እያሳየን እንመክራቸው ነበር። ሆኖም ግን፣ ሙያዊ ትችቶችን በፀጋ ተቀብሎ ራስን የማረም ዝግጁነት ትልቅ ፈተና ሆኖብናል።” ስትል ተናግራ እንደነበር አይዘነጋም።

ታድያ ስህተቶች ያሉ እና የሚኖሩ እንደመሆናቸው ስህተቶቹን ማረም የሚጀምረው ስህተቶች መኖራቸውን ከማመን ይነሳል ፤ ነገር ግን ከብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ የሚቀርቡ በማስረጃ የተደገፉ ገንቢ ሃሳቦችን ግን ለመቀበል ዳተኝነት መስተዋሉ የሚያስተዛዝብ ነው ፤ ፀሐይ የሞቀው ዓለም ያወቀው ስህተቶች እየፈፀሙ አይ ልንተች አይገባም የሚለው መርህ አልባ አካሄድ መታረም አለበት። አዎ ዳኝነታችን እጅግ ደካማ ነው ፤ ለዚህ ደግሞ አጠቃላይ የእግር ኳሱ ተዋንያን የሚወስዱት ድርሻ እንዳለ ሆኖ ዳኞቻችን ደግሞ የድርሻቸው መውሰድ የግድ ነው በተለይ ደግሞ ገሃድ የወጡ ቀላል የሚመስሉ ስህተቶች ሲፈጠሩ ከዳኞቹ ውጭ ሃላፊነት መውሰድ እና መተቸት የሚገባው አካል አይኖርም።

ከዚህ ባሻገር ግን ስህተቶችን ለመቀነስ አለም ዳኝነትን በቴክኖሎጂ መደገፍ ከጀመረ ሰንብቷል ፤ እኛ ካለብን የአቅም ውስንነት አንፃር ለቴክኖሎጂዎች እሩቅ ብንሆን እንኳን ሌሎች አማራጮችን ለመሞከር የሄድንበት ርቀት እጅግ ደካማ ነው።ለአብነትም ከጎል ጀርባ ተጨማሪ ሁለት ዳኞችን መመደብ ምንም እንኳን ዓለም በአንድ ወቅት ተጠቅሞ አሁን ላይ የተወዉ አማራጭ ቢሆን ከእኛ ችግር አንፃር ጊዜያዊ መፍትሔ ሊሰጥ እንደሚችል ይታመናል።

ሌላው ምንም እንኳን ቅጣት ነገሮችን ይለውጣል ተብሎ ባይታመንም መሰል ተራ ስህተቶችን የሚፈፅሙ ዳኞች ላይ ጠንካራ የቅጣት በትር ማሳረፍ የጠፋውን ውጤት ሆነ የተጎዳውን ተጫዋች ባይክስም ለቀጣይ ግን ሌሎች ዳኞች ይበልጥ ትኩረት እንዲያደርጉ ያግዛል።

እግር ኳስ መቼም ከስህተት የፀዳ ሊሆን እንደማይችል ይታወቃል ፤ ነገርግን እነዚህን ስህተቶች መቀነስ ግን የግድ ይላል።ይህን ለማድረግ ታድያ የዳኞቻችንን አቅም ማሳደግ ፣ የዳኞች ምደባ ስርዓታችንን መመርመር እንዲሁም ጠንካራ የሆነ የድጋፍ እና ክትትል ስርዓት መዘርጋትን ጨምሮ የዳኝነት አሰጣጡን የሚያግዙ ሌሎች ተጨማሪ አሰራሮችን (ቴክኖሎጂዎችን) ተግባራ ለማድረግ ጥረት የግድ ይላል ይህ ካልሆነ እና መሰል ተራ ስህተቶችን መታዘባችን የሚቀጥል ከሆነ የእግር ኳሳችንን ምስል ላይ ጥላ እንዳያጠላ ስጋትን ያጭራል።