አርባምንጭ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ የመጀመሪያውን ዙር በአቻ ውጤት አጠናቀቁ

አዞዎቹ እና ብርቱካናማዎቹ ያገናኘው በአዲስ አበባ የተደረገ የዕለቱ ብቸኛ ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ድሬዳዋ ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱበት እንዲሁም በርከት ያሉ ሙከራዎች የተደረገበት ነበር።
በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በተጀመረው ጨዋታ ላይ አዞዎቹ ጄሮም ፊሊፕ በራሱ ጥረት አግኝቶ ባደረጋት እንዲሁም ቡታቃ ሸመና ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል አክርሮ በሞከራት ኳስ ግብ ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ብርቱካናማዎቹ በበኩላቸው አቤል ነጋሽ ከመሐመድ ኑር ናስር የተቀበላትን ኳስ ተጠቅሞ ባደረጋት ሙከራ ጥቃታቸው ከጀመሩ በኋላ አቤል ነጋሽ አሻምቶት አብዱሰላም የሱፍ ባደረገው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ እና አስራት ቱንጆ በግሩም መንገድ የተሻገረችውን ኳስ ተጥቅሞ በፈጠራት አጋጣሚ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር።

በአጋማሹ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስም ሆነ ሙከራዎች በማድረግ ረገድ ብርቱካናማዎቹ ብልጫ መውሰድ ቢችሉም ቀድመው ግብ ማስቆጠር የቻሉት ግን አዞዎቹ ናቸው፤ አሸናፊ ተገኝ ከግራ መስመር አሻምቷት ታምራት ኢያሱ በግምባሩ ወደ ግብነት የቀየራት ኳስም አርባምንጭ ከተማን መሪ ያደረገች ግብ ነች። ሆኖም የአዞዎቹ መሪነት የቆየው ለስድስት ደቂቃዎች ብቻ ነበር፤ በ38ኛው ደቂቃ ላይ ድልአዲስ ገብሬ ከግራ መስመር አሻምቷት አቤል ነጋሽ በግንባሩ ያስቆጠራት ኳስም ብርቱካናማዎቹን አቻ ማድረግ የቻለች ግብ ነች።

ሁለተኛው የጨዋታ ምዕራፍ ከመጀመሪያው አጋማሽ ፍፁም የተለየ መልክ የነበረው ሲሆን ደካማ የማጥቃት እንቅስቃሴ የታየበት እና በሙከራዎች ያልታጀበ ነበር። በአጋማሹ ሁለቱም ቡድኖች የፊት መስመር እንቅስቃሴያቸውን ለማሻሻል የተጫዋቾች ለውጥ ማድረግ ቢችሉም ዓብዱሰላም የሱፍ በአጋማሹ የመጀመሪያ እና የመጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ከግራ መስመር ያደረጋቸው እና በግብ ጠባቂው ኢድሪሱ ኦጎዶጆ ከተመለሱ ሁለት የግብ አጋጣሚዎች ውጭ ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳይደረግበት ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

