23ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ በሚደረጉ አራት መርሐግብሮች ይቀጥላል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ባህርዳር ከተማ ከ ነጌሌ አርሲ
በሀያ ሰባት ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ባህርዳር ከተማዎች ከተከታታይ ሽንፈቶች ለማገገም ሰጎኖቹን ይገጥማሉ። በመደዳ አርባምንጭ ከተማ እና በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት የገጠማቸው የጣና ሞገዶቹ በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት ከማስተናገዳቸው በተጨማሪ በቅርብ ሳምንታት መጠነኛ መቀዛቀዞች ተስተውሎባቸዋል። በተለይም በተከታታይ መርሐ ግብሮች መረቡን ሳያስደፍር ከወጣ በኋላ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሰባት ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍላቸው በቀደመ ብቃቱ መዝለቅ አልቻለም። በዛሬው ጨዋታ ድል ለማድረግም የኃላ ክፍሉ ማጠናከር እንዲሁም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ማገናኘት የተሳነው የፊት መስመራቸው ማሻሻል ይኖርባቸዋል።
በሰላሣ ሰባት ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ነጌሌ አርሲዎች ከመሪው ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ለማጥበብ የሚያስችላቸውን ድል ለማግኘት ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። ሰጎኖቹ መሪው ሲዳማ ቡናን ያሸነፉበት ጨምሮ ሦስት ተከታታይ ድሎች ካስመዘገቡ ወዲህ ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች ሙሉ ነጥብ ማስመዝገብ አልቻሉም። ቡድኑ በመርሐ ግብሮቹ ማግኘት ከሚገባው ዘጠኝ ነጥብ ሰባቱን ጥሎ ሁለቱን ብቻ ማሳካቱም ከመሪው በአምስት ነጥብ እንዲርቅ አድርጎታል። ከዚህ አካሄድ ተላቆ ወደ ድል መንገድ ለመመለስም ሙሉ ነጥብ ባላገኘባቸው የመጨረሻዎቹ ሦስት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ ያስቆጠረውን የማጥቃት ክፍሉን ማሻሻል ግድ ይለዋል።
ባህርዳር ከተማ ማንያዘዋል ካሳ በቅጣት አማኑኤል ገብረሚካኤልን ደግሞ በጉዳት ዛሬ አያገኝም።
ነጌሌ አርሲዎች በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ያለው ዓብዱልባሲጥ ከማልን አያሰልፉም፤ ዳዊት ተፈራ ደግሞ የአንድ ጨዋታ ቅጣቱን ጨርሶ ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል።
ሁለቱም ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ያደረጉት ጨዋታ 0 ለ 0 ተጠናቋል።
ሽረ ምድረ ገነት ከ ፋሲል ከነማ
በሀያ ስድስት ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሽረ ምድረ ገነቶች ካሉበት የስጋት ቀጠና ለማምለጥ ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ። በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ ሦስት ጨዋታዎች አንድ ድል እና ሁለት ሽንፈቶች ያስተናገዱት ሽረዎች ውጤቶቹን ተከትሎ ወደ ስጋት ቀጠናው ይበልጥ ቀርበዋል። ከወራጅ ቀጠናው በሁለት ነጥብ ርቀት የሚገኘው ቡድኑ አሁን ካለበት ሁኔታ ለመውጣትም የቀደመው ወጤታማ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወቱን መመለስ እንዲሁም ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች በአምስቱ ኳስና መረብ ማገናኘት ተስኖት ሁለት ግቦችን ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት ጥምረቱን ማሻሻል ይኖርበታል።
በሰላሣ ሦስት ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፋሲል ከነማዎች ከሰሞነኛው አስከፊ አካሄድ የሚያወጣቸው ወሳኝ ድል ለማግኘት ይፋለማሉ።
ከኢትዮጵያ መድን ጋር አቻ እስከ ተለያዩበት የ19ኛው ሳምንት ጨዋታ ድረስ በሊጉ አንድ ሽንፈት ብቻ በማስተናገድ ከዘለቁ በኋላ ባደረጓቸው አራት ጨዋታዎች በመደዳ ሽንፈት ያስተናገዱት ዐፄዎቹ በተከታታይ ከገጠሟቸው ሽንፈቶች አገግመው ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ለመመለስ በብዙ ረገድ ተሻሽለው መቕረብ ይጠበቅባቸዋል።
በተለይም እስከ ውድድር ዓመቱ አጋማሽ ድረስ በሊጉ ዝቅተኛው የግብ መጠን በማስተናገድ ቀዳሚ የነበረውና ባለፉት አራት ጨዋታዎች 7 ግቦች ያስተናገደው የተከላካይ ክፍላቸው ሁለተናዊ ለውጥ ይሻል።
ሽረ ምድረ ገነት ጉዳት ላይ ካለው ጎይትኦም ነጋ በተጨማሪ በመጨረሻው ጨዋታ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣውን ሪችሞንድ አይ አያሰልፍም። በፋሲል ከነማ በኩል ያለውን መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
የተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት ጨዋታ ሳይጨምር በታሪካቸው 5 ጊዜ የተገናኙት ክለቦቹ ፋሲል ከነማ 2 ጨዋታ ሲያሸንፍ ሦስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። ፋሲል ከነማ 6 ግቦች ሲያስቆጥር ስሑል ሽረ 2 ግቦች አስቆጥሯል።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በሀያ ስምንት ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ድሬዳዋ ከተማዎች ከሰንጠረዡ አካፋይ ከፍ የሚያደርጋቸውን ነጥብ ለማግኘት ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። እጅግ አዝናኝ እና ብርቱ ፉክክር በተደረገበት የመጨረሻ ጨዋታቸው መቐለ 70 እንደርታን ሁለት ለአንድ አሸንፈው ከስጋት ቀጠናው ፈቀቅ ማለት የቻሉት ብርቱካናማዎቹ በወራጅ ቀጠናው አከባቢ ካሉ ክለቦች ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ከፍ አድርገው መጠነኛ እፎይታ ለማግኘት ዛሬ ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ። ብርቱካናማዎቹ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል መመለሳቸው እንዲሁም የማጥቃት አጨዋወታቸው በሂደት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ማሳየት መጀመሩ እንደ አወንታ የሚነሳላቸው ነጥብ ሲሆን በመጨረሻው ጨዋታ ተጋለጭ የነበረው እና በርከት ያሉ ሙከራዎች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃቸታቸው ግን ውስን ማሻሻያዎችን ይሻል።
በሀያ አራት ነጥቦች 18ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በጊዝያዊነት ከገቡበት ወራጅ ቀጠና ለመውጣት ድል ማድረግ አስፈላጊያቸው ነው። ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ሁለተኛውን ዙር ፋሲል ከነማን ሦስት ለአንድ በማሸነፍ ቢጀምሩም ቀጥለው በተካሄዱ ጨዋታዎች ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች አስተናግደዋል። ውጤቶቹን ተከትሎም ደረጃቸው አሽቆልቁሎ አሁን በወራጅ ቀጠናው ለመቀመጥ ተገደዋል። ከዚህ አካሄድ ለመውጣትም በሊጉ በርከት ያሉ ግቦች በማስተናገድ ቀዳሚ የሆነው እና ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦች ያስተናገደው የመከላከል አደረጃጀታቸ ላይ ስር ነቀል ለውጥ ማድረግ ግድ ይላቸዋል።
በንግድ ባንክ በኩል አዲስ ግደይ እና ካሌብ አማንክዋህ ከጉዳታቸው አገግመው ለጨዋታው ዝግጁ ሲሆኑ የድሬዳዋን የቡድን ዜና ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 17 ጊዜ ሲገናኙ ድሬዳዋ ከተማ 6 ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በተመሳሳይ 6 ጊዜ ድል ሲያደርግ 5 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። 33 ጎሎች በተቆጠሩበት የእርስ በርስ ግንኙነት ታሪክ 2 ጊዜ ብቻ ግብ ሳይቆጠር የተጠናቀቀ ሲሆን ባንክ 18፣ ድሬ 15 ጎሎችን አስቆጥረዋል።
ኢትዮጵያ መድን ከ ሀድያ ሆሳዕና
በሀያ አራት ነጥብ 17ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ኢትዮጵያ መድኖች በወራጅ ቀጠናው የነበሩ ሁለት ቡድኖች ነጥብ ማስመዝገባቸውን ተከትሎ በአደገኛው ቀጠና ውስጥ ገብተዋል። የዛሬው ጨዋታም ነጥባቸውን 27 በማድረስ ደረጃቸውን ለማሻሻል እያለሙ የሚያደርጉት እንደመሆኑ ወሳኝ ነው። ሁለተኛውን ዙር በአዳማ ከተማ ሽንፈት በማስተናገድ ቢጀምሩት ቀጥለው በተካሄዱት ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስን አሸንፈው ከሸገር ከተማ ጋር ነጥብ የተጋሩት ኢትዮጵያ መድኖች በቅርብ ሳምንታት ተደጋጋሚ የአቻ ውጤቶች ማስመዝገባቸውን ተከትሎ ደረጃቸው እንዲያሽቆለቁል ሆኗል። ወላይታ ድቻን ካሸነፈበት የ14ኛ ሳምንት ጨዋታ በኋላ በተካሄዱ ስምንት ጨዋታዎች አምስት የአቻ ውጤቶች፤ አንድ ድል እና ሁለት ሽንፈቶች የገጠሙት ቡድኑ ከአንድ ጨዋታ ዳግም ወደ ድል ለመመለስ በስድስት ጨዋታዎች ኳስና መረብ ሳያገናኝ ከዘለቀ በኋላ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ተሻሽሎ አራት ግቦችን ያስቆጠረው የማጥቃት አጨዋወቱን ይበልጥ ማጎልበት ይጠበቅበታል።
በሀያ ስምንት ነጥብ 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ሀድያ ሆሳዕናዎች ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ የሚያስጠጋቸውን ድል ፍለጋ ወደ ጨዋታው ይቀርባሉ። በሁለተኛው ዙር በተካሄዱ ሦስት ጨዋታዎች ሦስቱም የውጤት ዓይነቶች በእኩሌታ ያስመዘገቡት ነብሮቹ ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር ከስጋት ቀጠናው ይበልጥ ለመራቅ ዛሬ ወሳኝ ጨዋታ ያከናውናሉ። የዛሬው ተጋጣሚያቸውም ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ የሚጠበቅ ቡድን እንደመሆኑ በሁሉም ረገድ ተሻሽለው መቅረብ ግድ ይላቸዋል። በተለይም ባለፉት ሰባት መርሐ ግብሮች በአንድ ጨዋታ ከአንድ ግብ በላይ ማስቆጠር ያልቻለው የፊት መስመራቸው መሻሻል ይኖርበታል።
በኢትዮጵያ መድን በኩል ዋንጫ ቱት እና ረመዳን ሁሴን በጉዳት ምክንያት የዛሬው ጨዋታ የሚያልፋቸው ተጫዋቾች ናቸው። በሀዲያ በኩል ሙሴ ካቤላ በቅጣት ምክንያት አይኖርም።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ 7 ጊዜ ተገናኝተዋል፤ ኢትዮጵያ መድን 5 ጊዜ ሲያሸንፍ ሀዲያ ሆሳዕና በአንድ ጨዋታ አሸንፎ የተቀረው አንድ ጨዋታ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር። 15 ግቦች በተቆጠሩበት ግንኙነት ኢትዮጵያ መድን 9 ግቦችን ሲያስቆጥር፤ ሀድያ ሆሳዕና ደግሞ 6 ግቦችን አስቆጥረዋል።

