በሁለተኛው የኢትዮጵያ ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ወልዋሎ መቻልን በመለያ ምት 5 ለ 4 አሸንፎ ግማሽ ፍፃሜውን የተቀላቀለ ሁለተኛ ቡድን ሆኗል

ሁለት የፕሪምየር ሊግ ክለቦች ባገናኘው የኢትዮጵያ ዋንጫ የሩብ ፍፃሜ ሁለተኛ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ መቻሎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ከመውሰዳቸውም በተጨማሪ ተከታታይ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉበት ነበር።
ገና በ9ኛው ደቂቃ ኮሊንስ ኮፊ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል አሻምቶት የወልዋሎው ግብ ጠባቂ በአግባቡ ባለመቆጣጠሩ መሐመድ አበራ ያደረገው እና ግብ ጠባቂው በድጋሚ ባሳየው አስደናቂ ቅልጥፍና ቀዳሚ ሙከራ ያደረጉት መቻሎች ቀጥለውም ግሩም ሐጎስ ከቅጣት ምት አክርሮ መቶት በግቡ አግዳሚ በተመለሰ ኳስ መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር። በአንጻሩ ወልዋሎዎች በመቻሎች ብርቱ ጫና ምክንያት ወደ ራሳቸው የግብ ክልል አፈግፍገው በመከላከል ላይ ተጠምደው በአጋማሹ ይህ ነው የሚባል ግልጽ የግብ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ አጋማሹ ያለ ግብ ተገባዶ ለዕረፍት አምርተዋል።

ሁለቱም ቡድኖች በተሻለ አቀራረብ ተመልሰው ብርቱ ፉክክር ባደረጉበት ሁለተኛው አጋማሽ ቀዳሚ ለመሆን በፈጣን ሽግግር ለማጥቃት ጥረት ቢያደርጉም በርከት ያሉ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ግን ማድረግ አልቻሉም። ቡድኖቹ ጥንቃቄ ላይ ባመዘነ አጨዋወት በመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ለመፍጠር በተንቀሳቀሱበት አጋማሽ ላይ ግሩም ሐጎስ ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ከቆመ ኳስ ያደረገው እና የግቡ አግዳሚ ታኮ የወጣው ሙከራም ተጠቃሽ ነው።

መደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መጠናቀቂያ ላይ የቢጫ ለባሾቹ አምበል ፍሬው ሰለሞን በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣበት ክስተት ሲጠቀስ ጭማሪ ደቂቃዎች ላይ መቻሎች ለግብ የቀረቡ ዕድሎችን ፈጥረው ሳይጠቀሙበት ከቀሩ በኋላም ጨዋታው ያለ ግብ ተጠናቆ ወደ መለያ ምት አምርተዋል። አሸናፊው ለመለየት በተሰጠው እና አጓጊ ፉክክር በተደረገበት መለያ ምትም ወልዋሎዎች 5ለ4 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

