ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲና ኢትዮጵያ መድን ያገናኘው ጨዋታ በራስ ላይ በተቆጠሩ ግቦች አንድ ለአንድ በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ እንደተጀመረ የተሻለ የጨዋታ ፍሰት የነበራቸው ኢትዮጵያ መድኖች የነበራቸውን የኳስ የበላይነት ወደ ግብ ለመቀየር የፈጀባቸው ሰባት ደቂቃዎች ብቻ ነበር። በሰባተኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ማራኪ ቅብብል የተመሰረተውን ማጥቃት ተከትሎ ብሩክ በላቸው ያመቻቸውን ኳስ አልፍሬድ ንኩሩንዚዛ ወደ ውስጥ ሲያሻግር ኳሷም የወልዋሎውን ተከላካይ ጌቱ ኃይለማርያም ላይ ተጨርፋ መረብ ላይ በማረፏ መድኖችን ቀዳሚ ማድረግ ችላለች።

ይሁን እንጂ ወልዋሎ ዓዲግራቶች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም። በ12ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ ኮንኮኒ ሃፊዝ በግንባሩ ገጭቶ የሞከረውን ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ቢመልሰውም በቅርብ ርቀት ላይ የነበረው ዳዊት ገብሩ የተመለሰችውን ኳስ በድጋሚ ሲመታ ለማውጣት የሞከረው እስማኤል አብዱልጋኒዩ ዕድለኛ ሳይሆን ቀርቶ ወደ ራሱ ግብ አስቆጥሯታል። ይህች ግብ ቢጫ ለባሾቹን ወዲያውኑ ወደ ጨዋታው በመመለስ የመጀመሪያውን አጋማሽ በአቻ ውጤት እንዲጠናቀቅ አድርጋለች።

ሁለተኛው አጋማሽ ላይ በኳስ እንቅስቃሴ ረገድ በመጠኑም ቢሆን ወልዋሎ ዓዲግራቶች የተሻሉ የነበሩ ቢሆንም በስተመጨረሻ ደቂቃ የወልዋሎ ተጫዋች እንዳልካቸው ጥበቡ ካባከነው አስቆጪ እድል ውጪ ሌላ ሙከራ ሳያስመለክተን ጨዋታው በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

