ከቀናት በፊት መቻል ውል ያራዘመላቸው የሁለቱ ተጫዋቾች የዝውውር ሂደት ዕክል እንደገጠመው ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ለ2019 የኢትዮጵያ ሲቢኢ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ቅድመ ዝግጅት በመጀመር ምንም እንኳን የዘንድሮ የዘውውር ሂደቱ በይፋ ባይከፈትም ክለቦች አስቀድመው የአሰልጣኞችን የተጫዋቾች ዝውውር እያካሄዱ ይገኛል። በዚህ መነሻነት ከትናት ወዲያ መቻል ስፖርት ክለብ የስድስት ተጫዋቾችን ውል በማራዘም እና የሦስት አዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም ቡድኑን የማጠናከር ስራዎች እየሰራ ይገኛል።
ይሁን እንጂ ክለቡ ውል ያራዘሙ ተጫዋቾችን ለማፀደቅ ትናንት ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቢሮ ቢያቀናም በተለይ የሁለቱ ተጫዋቾችን ውል በይፋ እንዳይፈፀም እክል እንደገጠመው ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል። ውላቸው በመደበኛ ሂደት እንደማይራዘም የተነገራቸው ተጫዋቾች አብዱልከሪም ወርቁ እና ዓለምብርሃን ይግዛው ሲሆኑ ምክንያቱ ደግሞ ሁለቱ ተጫዋቾች አስቀድመው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ቅድመ ስምምነት መፈፀማቸው ሪፖርት በመቅረቡ እንደሆነ አውቀናል። ይህንን ተከትሎ መቻልም ኢትዮጵያ ቡናም የተጫዋቾቹን ይሁኝታ ያገኙበትን ማስረጃ ለፌዴሬሽኑ ማስገባታቸው የታወቀ ሲሆን በዚህ ሂደትም ተጫዋቾቹ ምናልባት ጉዳዩን በስምምነት የማይፈቱት ከሆነ ቅጣት ሊጣልባቸው እንደሚችል ተነግሯል።
የሁለቱ ተጫዋቾች ማረፊያ የት ሊሆን ይችላል የሚለውን ሶከር ኢትዮጵያ በቀጣይ በዚህ ጉዳይ የሚኖሩ አዳዲስ ነገሮች ተከታትለን የምታቀርብ ይሆናል።

