​ሪፖርት | ዳዊት ፍቃዱ ደምቆ በዋለበት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ ወልዲያን ረቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ በሜዳው ወልዲያን አስተናግዶ 4-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ በጨዋታው ላይ በክረምቱ ዝውውር ሀዋሳን የተቀላቀለው ዳዊት ፍቃዱ የ2010 የውድድር ዘመን የመጀመሪያው ሐት-ትሪክን አስመዝግቧል፡፡

ወልዲያ በመጀመሪያ ሳምንት ጨዋታ በሜዳው አዳማ ከተማን 2-0 ሲያሸንፍ ግብ ያስቆጠረው አንዱአለም ንጉሴን በኤደም ኮድዞ ቀይሮ ወደ ለጨዋታው ሲቀርብ ሀዋሳ በበኩሉ ግብ ጠባቂው ሜንሳህ ሶሆሆን በተክለማሪያም ተክቶ፣ ያቡን ዊልያምን ወደ መጀመርያ 11 በመመለስ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡

እንደ አዲስ የተቋበመው የሀዋሳ ከተማ የደጋፊ ማህበር ለክለቡ ያበረከተው ትጥቅን በማስተዋወቅ በተጀመረው ጨዋታ ሁለቱም ክለቦች የተጠቀሙት ሰማያዊ መለያ መመሳሰል ትኩረትን የሳበ ጉዳይ ነበር፡፡ የሀዋሳ የተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶች የወልዲያ የተከላካይ ክፍልን በቀላሉ ሲፈራካክሱ ወልዲያ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያደረው ደካማ ጥረት በጨዋታው ላይ ጎልተው የታዩ ጉዳዮች ነበሩ፡፡

በጨዋታው መጀመሪያ በፈጣን የማጥቃት ሽግግሮች ወደ ወልዲያ የሜዳ ክልል መድረስ የቻሉት ሀዋሳዎች በ8 ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ግቦችን አስቆጥረው 2-0 መሪ መሆን ችለዋል፡፡ በሁለተኛው ደቂቃ ካሜሩናዊው አጥቂ ያቡን ዊሊያም ከታፈሰ ሰለሞን ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ የወልዲያ ተከላካዮች በቀላሉ ማለፍ ከቻለ በኃላ የሃገሩ ልጅ ኤምክሬል ቤሊንጌ ላይ ግብ አስቆጥሮ ሀዋሳን መሪ አድርጓል፡፡ በግቡ መቆጠር የተነቃቃቱ ባለሜዳዎቹ ባልተረጋጋው የወልዲያ የተከላካይ ክፍል ላይ ጫና ማሳደራቸውን በመቀጠል ታፈሰ በግሩም ሁኔታ በወልዲያ ተከላካዮች መሃከል አሾልኮ ያሳለፈለትን ኳስ ዳዊት ፍቃዱ በሚገባ ተጠቅሞ የሀዋሳን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል፡፡

ከሁለቱ ግቦች መቆጠር በኃላ ወልዲያዎች በሰለሞን ገብረመድህን ጥረት የመሃል ሜዳ ብልጫውን መውሰድ ችለዋል፡፡ ቢሆንም በሁለቱም ክለቦች መካከል የሚቆራረጡ ኳሶችን እና ወደ ግብ ለመሄድ በሚደረጉ ጥረቶች በሚጨናገፉ የአጨዋወቶች ምክንያት ኳስ በአብዛኛው በመሃለኛው የሜዳ ክፍያ ላይ ተወስና እንድትቀር ሆኗል፡፡ በ15ኛው ደቂቃ ተስፋዬ በቀለ በጥሩ አጨዋወት ያገኘውን እድል ሞክሮ ተክለማሪያም ያመከናት፣ ከሁለት ደቂቃዎች በኃላ ተክለማሪያም ኤደምን ለማስጣል ከግብ ክልሉ መውጣቱን ተከትሎ ሰለሞን ግብ ለማስቆጠር ቢሞክርም ኳስ ኢላማዋን ሳትጠብቅ ወደ ውጪ የወጣችበት ኳስ ከወልዲያ ሙከራዎች ተጠቃሾች ነበሩ፡፡ የመጀመሪያው አጋማሽም አስደንጋጭ የሚባል ሙከራ ሳያስተናግድ በሀዋሳ መሪነት ተጠናቋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ ወልዲያዎች ሰለሞንን በሐብታሙ ሸዋለም ቀይረው ወደ ሜዳ በማስገባት ውጤቱን ለመቀልበስ ጥረት ቢያደርጉም ይባሱኑ በመጀመሪያው አጋማሽ በተወሰነ መልኩ የነበራቸውን የመሃል ሜዳ ብልጫ በሀዋሳ ተነጥቀዋል፡፡
በ72ኛው ደቂቃ ቢያድግልኝ ኤልያስን በግብ ክልሉ አቅራቢ ኳስን የነጠቀው ዳዊት ግብ ጠባቂው ቤሊንጌን ጭምር አልፎ የሀዋሳን መሪነት ወደ ሶስት አሳድጓል፡፡ ሆኖም በግብ ጠባቂ ስህተት ወልዲያዎች ልዩነቱን ወደ አንድ ዝቅ ማድረግ ችለዋል፡፡ በ81ኛው ደቂቃ ኮትዲቯራዊው መሃመድ ሲላ ለተክለማሪም ኳስ ወደ ኃላ ቢመልስም ግብ ጠባቂው ከግብ ክልሉ ለማራቅ የመታው ኳስ ኤደም ተደርቦ በቀላሉ ለወልዲያ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

ከግቡ መቆጠር በኃላ ጥንቃቄን የወሰዱት ባለሜዳዎቹ ተጨማሪ  አንድ ግብ ማግኘት ችለዋል፡፡ ዳዊት በሳጥኑ ውስጥ ያገኘውን እድል ተጠቅሞ ሀዋሳ በሜዳው በግብ እንዲንበሸበሽ ሲያስችል አጥቂውም በፕሪምየር ሊጉ በውድድር ዘመኑ የመጀመሪውን ሐት-ትሪክ የሰራ ተጫዋች ሆኗል፡፡

ዳዊት ግቡን ካስቆጠረ በኋላ የሀዋሳው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና ተቀያሪ ወንበር ላይ የነበሩ ተጫዋቾች ሳይቀሩ ወደ እሱ በማምራት ደስታቸውን ገልፀዋል፡፡ ሀዋሳ ተጨማሪ አምስተኛ ግብ ማስቀጠር የሚችልበትን እድል ያቡን ዊልያም ቢያገኝም ቤሊንጌን ለማለፍ ባደረገው ያልተሳካ ጥረት እድሉን አምክኗል፡፡

የውድድር ዘመኑን በሽንፈት የጀመረው ሀዋሳ ወደ ማሸን የተለሰበትን ወሳኝ ድል ሲያስመዘግብ ወልዲያ በበኩሉ በመጀመሪያው ጨዋታ ያሳካውን ድል መድገም ሳይችል አራት ግቦች ተቆጥረውበታል፡፡ እስካሁን በሊጉ በተደረጉት 12 ጨዋታዎችም ብዙ ግብ ያስተናገደ ጨዋታ ሆኖ አልፏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *