​ሪፖርት |  ፋሲል የአመቱን የመጀመሪያ ሽንፈት በቅዱስ ጊዮርጊስ አስተናግዷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ላይ ሳይደረግ ተላልፎ የቆየው የፋሲል ከተማ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ዛሬ በፋሲለደስ ስታድየም ተካሂዶ ቻምፒዮኖቹ  2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።

ፋሲል ከተማ ያሳለፍነው ቅዳሜ መቐለ ከተማን ከገጠመው ስብስቡ ፍሊፕ ዳውዝን በሔኖክ ገምተሳ የተካ ሲሆን ኤፍሬም አለሙን በመስመር እንዲሁም ራምኬል ሎክን በመሀል አጥቂነት ተጠቅሟል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ጉዳት የገጠማቸው አዳነ ግርማ እና አበባው ቡታቆ በአብዱል ከሪም ኒኪማ እና መሀሪ መና ከመተካታቸው በቀር ከወልድያ ያለግብ የተለያየውን ስብስብ ይዞ ነበር ጨዋታውን የጀመረው። የፋሲሎቹ ራምኬል ሎክ እና ያስር ሙገርዋም በጨዋታው የቀድሞ ክለባቸውን ገጥመዋል።

ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ ወደ ስፍራው የተጓዙት የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ለፋሲል አቻዎቻቸው የሁለቱ ክለቦች አርማ ያረፈበትን የአፄ ቴዎድሮስ ምስል የያዘ ባነር አበርክተዋል።

ጨዋታው በጀመረበት ቅፅበት ነበር ጎል ያስተናገደው። ከግራ መስመር ተቀምቶ የተሻማን ኳስ የፋሲል ተከላካዮች በሚገባ ሳያርቁት አግኝቶ በሀይሉ አሰፋ ነበር ከመረብ ማገናኘት የቻለው። ኳስ ይዘው በመጫወት ወደ ቅዱስ ጊዮርጊሶች የሜዳ ክልል ለመግባት ሲሞክሩ የነበሩት ፋሲል ከተማዎች የጊዮርጊስን የተከላካይ መስመር በቀላሉ ሰብረው መግባት አልቻሉም። የፈረሰኞቹ የአማካይ መስመር በተለይም ምንተስኖት አዳነ ወደ ግራ መስመር ያደላ የመከላከል ሽፋን የባለሜዳዎቹን የቀኝ መስመር ጥቃት ክፍተት እንዳያገኝ አድርጓል። ፋሲሎች የሚታወቁበት ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ጉልበቱ ተዳክሞ በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ የቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ እና የአማካይ ክፍል የመከላከል ቅርፁን ከያዘ በኃላ በተለይ ከዳዊት እስጢፋኖስ ይነሱ የነበሩ ኳሶች የታሰበላቸውን አላም ማሳካት አልቻሉም።  ቡድኑ ያደረጋቸው ጥቂት ሙከራዎችም በራምኬል ሎክ አማካይነት ከሳጥን ውጪ የተደረጉ ነበሩ። ከወትሮው እጅግ ጎልቶ የታየው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋቾች በተቃራኒ ሜዳ ላይ ያሳድሩት የነበረው ጫና ለድላቸው ዋነኛ ምክንያት ነበር። ሁሉም የቅዱስ ጊዮርጊስ ሙከራዎችም በተመሳሳይ አካሄድ ከፋሲሎች የሚቀሙ ኳሶችን መሰረት አድርገው የተገኙ ነበሩ። በተለይም 25ኛው ደቂቃ ላይ ኢብራሂማ ፎፋና በፋሲል ሳጥን አቅራቢያ ከተቀማ ኳስ በቀጥታ ሞክሮ የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። በዚህ ረገድ አቡበከር ሳኒ ሰፊ የሜዳ ክልል በመሸፈን የፋሲል ተከላካዮች ኳስ በቀላሉ እንዳይጀምሩ ያደርግ የነበረው ጥረት በጉልህ የሚታይ ነበር። ተጨዋቹ ተቀይሮ በወጣበት ወቅትም የአፄዎቹ ደጋፊዎች ሙገሳን ቸረውታል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ተነቃቅተው የታዩት ፋሲሎች በራምኬል ሎክ እና ያስር ሙገርዋ አማካይነት ከርቀት ጥሩ የሚባሉ ሙከራዎችን አድርገዋል። ሆኖም እንደመጀመሪያው አሃማሽ ሁሉ አሁንም ቅብብሎቻችፕው የጊዮርጊስን የተከላካይ መስመር ማስከፈት የሚችሉ አልነበሩም። የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮች በሚገባ ሳይደራጁ ወደ ሳጥኑ መግቢያ ላይ በቀረቡባቸው አጋጣሚዎችም ንፁህ የግብ ዕድሎችን በብዛት መፍጠር አልቻሉም። ይህ ጥረታቸው ፍሪያማ ሆኖ ሮበርት ኦድንካራን መፈተን ከመጀመራቸው በፊትም 58ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ጎል አስተናግደዋል። እንደመጀመሪያው ሁሉ በድጋሜ በግራ መስመር ቅዱስ ጊዮርጊሶች የነጠቁትን ኳስ በሀይሉ አሰፋ አሳልፎለት በግማሽ ጨረቃው ላይ ይገኝ የነበረው አብዱልከሪም ኒኪማ በቀጥታ በመምታት አስቆጥሯል። ከዚህ በኃላ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ለተከላካይ መስመራቸው የሚሰጡት ሽፋን ጨምሮ ታይቷል። ሆኖም በመልሶ ማጥቃት 72ኛው ደቂቃ በምንተስኖት አዳነ እና አቡበከር ሳኒ ቅብብል ጥሩ የግብ አጋጣሚ የፈጠሩ ሲሆን ተቀይሮ የገባው ሲዴ ኬይታም 82ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውስጥ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ችሎ ነበር። ሁለተኛው ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላም ፋሲሎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ማግኘት ባይቸግራቸውም ውጤቱን ማጥበብ የሚችሉበት አጋጣሚ ግን አልተፈጠረም። ሆኖም የተሻለ ሲንቀሳቀስ የነበረው ኤፍሬም አለሙ 79ኛው እና 90ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ችሏል። ያም ቢሆን ፋሲሎች ወደ ጊዮርጊስ የመከላከል ወረዳ ውስጥ ዘልቀው መግባት ሳይችሉ ጨዋታው ተጣናቋል። በውጤቱም ፋሲል ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሸነፈ ሲሆን ሮበርት ኦድንካራ እና ቅዱስ ጊዮርጊስም ለተከታታይ ሰባት ጨዋታዎች መረባቸውን ሳያስደፍሩ ወጥተዋል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ምንተስንምት ጌጡ – ፋሲል ከተማ

እናሸንፋለን ብለን አስበን ነበር። ከእረፍት በኃላ ብዙ የግብ ዕድሎችን አግኝተን ነበር። ማስቆጠር አልቻልንም። መሸነፍ ማለት መውደቅ አይደለም። ከዚህ ሽንፈታችን በመነሳት ምንድነው የሌለን ብለን መጠየቅ አለብን። በተለይም ከወገብ በላይ ያለው የቡድናችን ክፍል ላይ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል።

ም/አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ጨዋታው ጥሩ ነበር። እኛ በምንፈልገው መንገድ ሄዷል። ትንሽ ውጥረት የበዛበት ጨዋታ ነው። ጨዋታውን ተቆጣጥረን ጎል አግብተን የተጋጣሚያችንን ሁኔታ አስቸጋሪ ለማድረግ ፈልገን ነበር። ተሳክቶልናል። የምንፈልገውን ውጤትም አግኝተናል። ውጤቱ  ደደቢት ይበልጥ እንዳይርቀን እና ለደጋፊዎቻችንም ክብር ወሳኝ ነበር።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *