ድሬዳዋ ከተማ የ28ኛ ሳምንት ጨዋታውን ለማድረግ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጧል

የአርባምንጭ ከተማ እና የወልዋሎ ዓ.ዩ ተስተካካይ ጨዋታዎች እንዲካሄዱ የጠየቀው ድሬዳዋ ከተማ ይህ የማይሆን ከሆነ የ28ኛ ሳምንት ጨዋታውን የማያደርግ መሆኑን ለፌዴሬሽኑን በደብዳቤ አሳወቋል።

ከ25ኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች መካከል ደደቢት ከአርባምንጭ ከተማ እንዲሁም በ27ኛው ሳምንት ደግሞ ወላይታ ድቻ ከወልዋሎ ዓ.ዩ ይገናኙ የነበሩባቸው ጨዋታዎች በተለያዩ ምክንያቶች ሳይካሄዱ መቅረታቸው ይታወሳል። በዚህ ጉዳይ ቅሬታ የተሰማው የምስራቁ ክለብም የጨዋታዎቹ አለመደረግ ላለመውረድ በሚደረገው ትንቅንቅ ውስጥ በቀጣይ በሚኖሩት ጨዋታዎች ላይ አንዱ የአንዱን ውጤት በመጠበቅ ስሌት ውስጥ ስለሚገባ ተስተካካይ ጨዋታዎቹ ከወዲሁ ተደርገው መጠናቀቅ እንዳለባቸው ለፌዴሬሽኑ ባስገባው ደብዳቤ ገልጿል።

ክለቡ ያለውን ቅሬታ በገለፀበት በዚሁ ደብዳቤ ” በተለያዩ ምክንያቶች የ25ኛው እና 27ኛው ሳምንት ጨዋታዎች መቋረጣቸው ይታወቃል። ሆኖም የፕሪምየር ሊጉ ውድድር ሊጠናቀቅ የቀረው የሦስት ሳምንት መርሀግብር በመሆኑ 28ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከመደረጋቸው በፊት እነዚህ ተስተካካይ ጨዋታዎች መደረግ እንዳለባቸው እያሳወቅን ተስተካካይ መርሀ ግብሮች ሳይጠናቀቁ ቀጣይ ጨዋታዎችን የማናደርግ መሆኑን ለኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እናሳውቃለን ” ብሏል ።