ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ድሬዳዋ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

ሌላኛው ቅድመ ዳሰሳችን ከነገ ተስተካካይ ጨዋታዎች መካከል አንዱ በሆነው የሲዳማ ቡና እና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።

በድሬዳዋ ከተማ በነበረው አለመረጋጋት ምክንያት ከ13ኛው ሳምንት የተላለፈው የድሬዳዋ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጨዋታ ነገ 09፡00 ላይ ይከናወናል። ጨዋታው ለሁለቱም ቡድኖች የመጨረሻ የ 15ኛ ሳምንት መር ሐ ግብርም ይሆናል። በሌላኛው ተስተካካይ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ ከመከላለያ ጋር ነጥብ መጋራት የቻለው ድሬዳዋ ከተማ አንድ ደረጃን ብቻ አሻሽሎ በ12ኝነት የተቀመጠ ሲሆን ነገ ድል ቢቀናው እንኳን ከ10ኛነት በዘለለ ዙሩን ማጠናቀቅ አይችልም። በመቐለው እና በመከላከያው ጨዋታ የቡድናቸው አጨዋወት በፈለጉት ደረጃ ላይ እንደማይገኝ የገለፁት አሰልጣኝ ስምዖን አባይ በነገው ጨዋታ ጉዳት ላይ የሚገኙት ፍቃዱ ደነቀ ፣ ሳሙኤል ዮሀንስ እና ሚኪያስ ግርማን እንደማይደርሱላቸው ታውቋል። በአንፃሩ ከመሀመድ ናስር ቀይ ካርድ ውጪ ተጨማሪ የጉዳት ዜና የሌለበት ሲዳማ ቡና ከመሪው መቐለ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሁለት ዝቅ ለማድረግ ከነገው ጨዋታ ሦስት ነጥቦችን ለማሳካት ይፋለማል። ሲዳማ በ 15ኛው ሳምንት ከሜዳው ውጪ ከወልዋሎ ጋር ነጥብ ከተጋራ አስር ቀናት በኋላ ነው ጨዋታውን የሚያከናውነው። በውድድር ዓመቱ አንድ ሽንፈት ብቻ የገጠመው ቡድኑ ነገም ይህን ክብሩን አስጠብቆ ከወጣ በመጀመሪያው ዙር ጥቂት ሽንፈት የገጠመው ክለብ መሆን ይችላል።

የእርስ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– ከቡድኖቹ 12 ግንኙነቶች ውስጥ ሲዳማ 5 ጊዜ ሲያሸንፍ 6 ጊዜ አቻ ተለያይተው ድሬዳዋ አንድ ጊዜ ብቻ አሸንፏል። ሲዳማ 10 ድሬዳዋ ደግሞ 5 ግቦችንም አስመዝግበዋል።

– የድሬዳዋ ብቸኛ ድል የተመዘገበው 2002 ላይ በመጀመርያ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸው ሲሆን ይርጋለም ላይ በተደረገው ጨዋታ 1-0 አሸንፎ ነበር።

– ድሬዳዋ ከተማ ከተማ ሜዳው ላይ ስድስት ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን ሦስት የሽንፈት ፣ ሁለት የድል እና አንድ የአቻ ውጤት አስመዝግቧል። የመጨረሻዎቹ ሁለት የሜዳው ጨዋታዎች በሽንፈት የተጠናቀቁ ነበሩ።

– ሲዳማ ቡና ከሀዋሳ ውጪ አምስት ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን ድል የቀናው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በቀሪዎቹ ጨዋታዎች ሦስቴ ነጥብ ሲጋራ አንድ ጊዜ ደግሞ ተሸንፏል።

ዳኛ

– ኃይለየሱስ ባዘዘው ይህን ጨዋታ በመሀል ዳኝነት የመምራት ኃላፊነት ተሰጥቷታል። አርቢትሩ በዳኘባቸው አምስት ጨዋታዎች ስምንት የማስጠንቀቂያ ካርዶች እና ሁለት የፍፁም ቅጣት ምቶችን ሰጥቷል። አርቢትሩ በያዝናው የውድድር ዓመት ሁለቱ ቡድኖች የተሳተፉበትን ጨዋታ አልመራም።

ግምታዊ አሰላለፍ

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ፍሬው ጌታሁን

ዘነበ ከበደ – አንተነህ ተስፋዬ – በረከት ሳሙኤል – አማረ በቀለ

ቢኒያም ፆመልሳን – ፍሬድ ሙሺንዲ

ገናናው ረጋሳ – ምንያህል ይመር – ሬምኬል ሎክ

ሀብታሙ ወልዴ

ሲዳማ ቡና (4-3-3)

ፍቅሩ ወዴሳ

ግሩም አሰፋ – ፈቱዲን ጀማል – ዳግም ንጉሴ – ሚሊዮን ሰለሞን

ግርማ በቀለ – ዮሴፍ ዮሃንስ – ዳዊት ተፈራ

ጫላ ተሺታ – ሀብታሙ ገዛኸኝ – አዲስ ግደይ


© ሶከር ኢትዮጵያ
በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *