ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ድል ተመልሶ ከመሪው ያለውን የነጥብ ልዩነቱን ቀንሷል

አዲስ አበባ ላይ ዛሬ በተደረገው የ20ኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን 2-0 መርታት ችሏል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ ሽረ ላይ ነጥብ ተጋርቶ ከተመለሰበት ጨዋታ ቅጣት ላይ በሚገኘው ሳላዲን በርጌቾ እና አሜ መሀመድ ምትክ ኢሱፍ ቡርሀና እና ሀምፍሬይ ሚዬኖን የተጠቀመ ሲሆን በተመሳሳይ ሁለት ለውጦች ያደረጉት ሲዳማዎችም አዳማን ከረቱበት ጨዋታ በአምስተኛ ቢጫ ካርድ ባልተሰለፈው ግርማ በቀለ እና ዳዊት ተፈራ ቦታ ተስፉ ኤልያስ እና ትርታዬ ደመቀን ተጠቅመዋል። ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞም በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ለተለዩት የቀድሞው ዳኛ እና ኮምሽነር መብራቱ አዲስ የህሊና ፀሎት ተድርጓል።

የመጀመሪያው አጋማሽ በአመዛኙ የባለሜዳዎቹ የበላይነት የታየበት ነበር። ሁለቱም ተጋጣሚዎች መሀል ሜዳ ላይ የተረጋጉ ቅብብሎችን በብዛት መከወን ባልቻሉበት በዚህ አጋማሽ የሜዳ ላይ ግጭቶችም ተበራክተው ታይተዋል። በቶሎ ኳሶችን ወደ መስመር በማሳለፍ ወደ ቀኝ አድልተው ጫና ፈጥረው የነበሩት ሲዳማዎች 7ኛው ደቂቃ ላይ ከግሩም አሰፋ በተነሳ ረጅም ኳስ ሀብታሙ ገዛኸኝ ከሳጥን ውስጥ ካደረገው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ በኋላ በማጥቃቱ ተቀዛቅዘው ታይተዋል። ወደ ፊት የሚላኩ ኳሶች ያልተመጠኑ መሆን እና የቡድኑ የአማካይ ክፍል በሽግግሮች ወቅት ይታይበት የነበረው መበታተን ደግሞ ለተወሰደባቸው ብልጫ ምክንያቶች ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው። ከዚህ ባለፈም የቡድኑ ተከላካዮች ከተጋጣሚ አጥቂዎች በሚፈጠሩባቸው ጫናዎች የሚሰሯቸው ስህተቶች ለሲዳማ ተጨማሪ የጥቃት ምንጭ ሆነውበታል።

ቅዱስ ጊዮርጊሶች እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ ኳስ ይዘው ባይጫወቱም ከኋላ ከሚነሱ ረጃጅም ኳሶቻቸው በተጨማሪ ከአማካዮቹ በቂ ሽፋን ሳያገኝ በቀረው የሲዳማ የተከላካይ መስመር መሀል በሚፈጠሩ ክፍተቶች ደጋግመው በሳጥን ውስጥ መገኘት ችለው ነበር። በተለይም አቤል ያለው 20ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ በኩል ሰብሮ ገብቶ ያመከነው እና 32ኛው ላይ ሚዮኔ ከሰነጠቀለት ኳስ ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ የሳተው በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ነበሩ። አቤል 21ኛው ደቂቃ ላይም ኢሱፍ ብርሀና በግራ በኩል ካደረሰው ኳስ ከቅርብ ርቀት ሞክሮ ተከላካዮች ተደርበውበታል። ሆኖም ተደጋጋሚ ዕድሎችን ያባከነው አጥቂው 35ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት ያሻገረው ኳስ በኢሱፍ ቡርሀና በግንባር ተገጭቶ ከሲዳማ መረብ ላይ አርፏል። ቅዱስ ጊዮርጊሶች ጨዋታው ወደ ዕረፍት ሊያመራ ሲልን ሪችራድ አርተር ከሄኖክ አዱኛ ተሻጋሪ ኳስ ባደረገው የግንባር ሙከራ ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀምር ሰንደይ ሙቱኩ እና ዳዊት ተፈራን ቀይረው በማስገባት የኋላ እና የመሀል ክፍላቸውን ለማስተካከል ጥረት ያደረጉት ሲዳማዎች መጠነኛ ለውጥ ቢታይባቸውም አሁንም የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን መፍጠር አልሆነላቸውም። ከኋላ በሚጣሉ ኳሶች ላይ ተመስርተው በግል ጥረታቸው አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ የነበሩት አዲስ ግደይ እና ሀብታሙ ገዛኸኝ እንቅስቃሴዎችም ፍሪያማ ካለመሆናቸው ባለፈ የመሀል አጥቂው መሀመድ ናስርም ተቀይሮ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ተነጥሎ ቆይቷል። በተደጋጋሚ በተጋጣሚያቸው ሳጥን ውስጥ እየተገኙ ሙከራዎችን ለማድረግ ከጫፍ ሲደርሱ ይታዩ የነበሩት ጊዮርጊሶችም የፈፅሟቸው በነበሩ ይቅብብል እና የሙከራ ውሳኔ ስህተቶች ምክንያት ጥረቶቻቸው የማዕዘን ምቶችን ከማስገኘት ባለፈ ፍቅሩ ወዴሳን የሚፈትኑ አልነበሩም።

አካላዊ ንክኪዎች እና ጉሽሚያዎች በተበራከቱበት ሁለተኛው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች 88ኛው ደቂቃ ላይ ወንድሜነህ ዓይናለም ከሳጥን ውጪ ካደረገው ሙከራ ሌላ ጠንካራ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም። ከዚህ ውጪ 72ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ግደይ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ ይዞ በመግባት ከማስቆጠሩ በፊት ኄኖክ አዱኛ ኳስ ያስጣለበት መንገድ ተገቢ አይደለም በማለት ፍፁም ቅጣት ምት ይገባናል በሚል ቅሬታቸውን ያሰሙት እንግዶቹ ከፌደራል ዳኛ እያሱ ፈንቴ ጋር ሰጣ ገባ ውስጥ ገብተው ጨዋታው ለአራት ደቂቃዎች ተቋርጧል። ነገሮች ተረጋግተው ሲቀጥልም 80ኛው ደቂቃ ላይ አሜ መሀመድ በተከታታይ ሁለት ኳሶችን ከሳጥን ውጪ ሲሞክር አንዱ በግቡ አግዳሚ ሌላኛው ደግሞ በፍቅሩ ጥረት ድነዋል። ሆኖም ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ፊርምፖንግ ሜንሱ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ሰንደይ ሙቱኩ ፍቅሩ ይደርስበታል በሚል በተዘናጋበት ቅፅበት አቡበከር ሳኒ ከኋላ በመግባት በግንባሩ አስቆጥሮ ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ አድርጓል።

ውጤቱን ተከትሎም ሲዳማ ቡና በ34 ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በ33 ነጥብቦች በነበሩበት የ3ኛ እና 4ኛ ደረጃ ላይ ረግተዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡