ሦስት አሰልጣኞች ለስልጠና ወደ አሜሪካ ያመራሉ

ብርሃኑ ባዩ፣ ብርሃኑ ግዛው እና አሥራት አባተ ለላሊጋ ስልጠና ወደ አሜሪካ ሲያመሩ ውበቱ አባተ ጉዞውን ሰርዟል።

ባለፉት ተከታታይ ዓመታት በርካታ አሰልጣኞች የተሳተፉበት ይህ የ “ላሊጋ ሜተድ” ስልጠና በዚ ዓመት ከካሊፎርንያ ግዛት ወደ ቺካጎ የቦታ ለውጥ ያደረገ ሲሆን ስልጠናውም ለሰባት ቀናት እንደሚቆይ ለማወቅ ተችሏል። ወደ ስልጠናው የሚያመሩ አሰልጣኞችም ላለፉት በርካታ ዓመታት ከኢትዮጽያ ንግድ ባንክ የሴቶች ቡድን ጋር ስኬታማ ጊዜ ያሳለፈው ብርሃኑ ግዛው፣ በዚህ ዓመት በአንደኛ ሊጉ ቢሾፍቱ ከተማ ቆይታ ያደረገው እና በሴቶች እግር ኳስ ጥሩ ውጤት ያለው አሥራት አባተ እንዲሁም በዚህ ወቅት ክለብ አልባ የሆነው የቀድሞ የኢትዮ ኤሌክትሪክ የወንዶች እና ሴቶች አሰልጣኝ ብርሃኑ ባዩ ናቸው።

ሌላው ወደ ስፍራው ያቀናል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የፋሲል ከነማ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ደግሞ ቡድኑን ለማዘጋጀት ጉዞውን ሰርዟል።
አሰልጣኙ ምንም እንኳ ከክለቡ ጋር ለመለያየት ደብዳቤ ቢያስገባም ቡድኑ ለአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ዋንጫ ለማዘጋጀት እና የአዛሙን ጨዋታ ለመምራት ጉዞውን ሰርዞ ወደ ባህርዳር አቅንቶ የቡድኑ ዝግጅት ይቀላቀላል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡