ቻምፒየንስ ሊግ | ካኖ ስፖርት አካዳሚዎች አመሻሽ ላይ የመጨረሻ ልምምዳቸውን አጠናቀዋል

የመቐለ 70 እንደርታ ተጋጣሚ ካኖ ስፖርት አካዳሚ የመጨረሻ ልምምዳቸው ሲያከናውኑ ዋና አሰልጣኙም ሃሳባቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል።

በመጀመርያው ዙር በሜዳቸው የኢትዮጵያው መቐለ 70 እንደርታን ሁለት ለአንድ አሸንፈው ለመልሱ ጨዋታ ትናንት ኢትዮጵያ የገቡት ካኖ ስፖርት አካዳሚዎች ዛሬ ጠዋት መቐለ በመግባት አመሻሽ ላይ በትግራይ ስቴድየም ልምምድ ሰርተዋል። ሳይጠበቅ ከተለመደው አሰራር ወጣ ብለው በመጨረሻው ልምምድ ረጅም ሰዓት የወሰደ እና ጠንከር ያለ ልምምድ የሰሩት ካኖዎች በከተማው በነበረው መጠነኛ ዝናብ ዘግይተው ነበር ልምምድ የጀመሩት።

በመጨረሻው ልምምዳቸው እንደአብዛኞቹ የአፍሪካ ቡድኖች የቆሙ ኳሶች እና ለመስመር አጨዋወት የሚረዱ ልምምዶች ሲሰሩ ከዛ በተጨማሪ ተጋጣሚን ተጭኖ የመጫወት ክህሎት የሚያዳብሩ (Pressing) ልምምዶችም በስፋት ሰርተዋል።

ከልምምዱ መጠናቀቅ በኋላ የኢንግሊዘኛ ቋንቋ ለመናገር የሚቸገሩት የካኖ ስፖርት ዋና አሰልጣኝ ዴቪድ ካስትሮ በመቐለ 70 እንደርታ ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ልባርጋቸው ምህረቱ አጋዥነት ለሚድያዎች አጭር ንግግር አድርገዋል።

አሰልጣኙም ለመሰል ውድድር እንግዳ መሆናቸውን ገልፀው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ለማሸነፍ እና ጥሩ ልምድ ለማግኘትም እንደሆነ ገልፀዋል። አሰልጣኙ ቀጥለውም በመቐለ እና በአዲስ አበባ ስለ ነበራቸው ቆይታ በጣም ደስተኛ መሆናቸው ሲገልፁ በወጣቶች የተገነባው ቡድናቸው በኢትዮጵያ የአጭር ጊዜ ቆይታው በመላው ቡድኑ ደስተኛ እንደሆነ ገልፀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡