ሴቶች ዝውውር | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጨዋች ማስፈረሙን ቀጥሏል

በአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመሩት ኢትዮጽያ ንግድ ባንኮች ዛሬ የአንድ ተጨዋች ዝውውር ሲያጠናቅቁ የነባር ተጨዋችም ውል አድሰዋል።

በዝውውር ገበያው ተቀዛቅዘው የነበሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በተከታታይ ቀናት ተጨዋቾችን ወደ ቡድናቸው እየቀላቀሉ ይገኛሉ። ዛሬ ረፋድም ወጣቱዋን አጥቂ ፎዚያ መሃመድን አስፈርመዋል። ከኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ በመውጣት ወደ አዲስ አበባ ከተማ አቅንታ የነበረችው ፎዚያ በግሏ ጥሩ ጊዜ ማሳለፏ ይታወሳል። ይህቺ ፈጣን አጥቂ በርካታ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጨዋቾችን ወደ ቡድኑ እየቀላቀለ ለሚገኘው ንግድ ባንክ አማራጭ ትሰጣለች ተብሎ ይጠበቃል።

ከፎዚያ በተጨማሪ ቡድኑ የሽታዬ ሲሳይንም ውል ከሰዓታት በፊት አድሷል። ለየካ ክፍለ ከተማ፣ ሴንትራል ዩኒቨርስቲ እና ኢትዮጵያ ቡና መጫወት የቻለችው ሽታዬ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ከቡድኑ ጋር ለመቆየት ነው ፊርማዋን ያኖረችው። ሽታዬ ለስምንት ዓመታት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቤት መጫወቷ አይዘነጋም።

ክለቡ ከዚህ በኋላ ተጫዋች የማስፈረም እቅድ እንደሌለው አሰልጣኝ ብርሀኑ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ