በውጪ ሊጎች የሚጫወቱ ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በዚህ ሳምንት …

በግብፅ ሊግ ዑመድ ኡክሪ ለአዲሱ ቡድኑ የመጀመርያ ግቡን ሲያስቆጥር የሽመልስ በቀለው ምስር ኤልማቃሳ ተሸንፎ የጋቶች ፓኖም ሀራስ ኤል ሁዳድ አቻ ተለያይቷል። ቢንያም በላይ የሚገኝበት የስዊድኑ ስሪያንስካ ደግሞ በሊጉ የመቆየት ተስፋው ያለመለመበትን ድል አስመዝግቧል።

በሦስተኛው ሳምንት ግብፅ ፕሪምየር ሊግ ቅዳሜ ዑመድ ኡክሪ የሚጫወትበት አስዋን በሜዳው በአልአህሊ 5-1 በተሸነፈበት ጨዋታ ብቸኛዋን ጎል አስቆጥሯል። በክረምቱ ስሞሀን ለቆ አስዋንን የተቀላቀለው ዑመድ በተጠባባቂነት ጨዋታውን ጀምሮ በ53ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባ ሲሆን በ67ኛው ደቂቃም በአዲሱ ክለቡ መለያ የመጀመርያ ጎሉን ማስቆጠር ችሏል።

እሁድ እለት ሌላው በአዲስ ክለብ የዘንድሮውን የሊግ ውድድር የጀመረው ጋቶች ፓኖም አዲሱ ቡድኑ ሀራስ ኤል ሁዳድ ከታንታ ጋር 1-1 ሲለያይ በተመሳሳይ እሁድ ሌላው የኢትዮጵያዊ ሽመልስ በቀለ የሚገኝበት ምስር አልማቃሳ በኤል ጎና 1-0 ተሸንፏል።

በስዊድን ሁለተኛው የሊግ እርከን (ሰፐርታን) የሚወዳደሩት እና ባለፉት ጨዋታዎች ተደጋጋሚ የሽንፈት እና የአቻ ውጤቶች ያስመዘገቡት ስሪያንሳካዎች በትናንትናው ዕለት በሜዳቸው አርግርይተ የተባለ ክለብ አስተናግደው ስታድለር ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ በማሸነፍ በሊጉ የመትረፍ ዕድላቸው አለምልመዋል።

ከረጅም ግዜያት በኃላ ኢትዮጵያዊው ቢንያም በላይ ወደ ፊት ስበው ያጫወቱት ስሪያንስካዎች የትናንትናው ጨዋታ ማሸነፋቸው ተከትሎ ብሮማፖጃካርና እና ኦስተርስ በልጠው በ25 ነጥቦች አስራ አራተኛ ላይ ሲቀመጡ በሊጉ ለመቆየትም ሁለት ዕድሎች ከፊታቸው ይገኛል።
ባለፈው ዓመት በመለያ ጨዋታ ወደ ሊጉ ያደገው ቡድኑ 13 እና 14 ደረጃ ይዞ ካጠናቀቀ ወደ መለያ ጨዋታ የሚያመራ ሲሆን ሌላው ዕድልም ቡድኑን በአምስት ነጥቦች በልጦ አስራ ሁለተኛ ደረጃ የሚገኘው ቫስተራስን በተቀሩት ጨዋታዎች በነጥብ በልጦ ሊጉን መጨረስ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ