ባህር ዳር ከተማ ላቋቋማቸው የሴት እና ወጣት ቡድኖች የአሰልጣኝ ቅጥር ፈፅሟል

ባህር ዳር ከተማ ዘንድሮ ለመሰረተው የሴቶች ቡድን እና ወጣት ቡድን የአሰልጣኝ ቅጥር ፈፅሟል።

ከወራት በፊት አዲስ ኮሚቴ አቋቁመው አደረጃጀታቸውን ለማሳደግ ስራዎችን ሲሰሩ የነበሩት ባህር ዳር ከተማዎች ከቀናት በፊት አዲስ ሊያቋቁሙት ላሰቡት ቡድን (የሴቶች እና ወጣት ቡድን) የአሰልጣኝ ቅጥር ለመፈፀም ማስታወቂያ ማውጣታቸው ይታወሳል። ክለቡ ሊያቋቁም ላሰበው የሴቶች ቡድን አሰልጣኝ ሰርካዲስ እውነቱ፣ ፍሬው ሃ/ገብርኤል እና እውነቱ ጣለው ለመጨረሻ የቃል እና የፅሁፍ ፈተና አልፈው ከትላንት በስቲያ ፈተናቸውን አድርገዋል።

በዚህም ሰርካዲስ እውነቱ የሴቶች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆና ተመርጣለች። የቀድሞ ዳሽን ቢራ ምክትል አሰልጣኝ የነበረችው እና የጥረት ኮርፖሬት ዋና አሰልጣኝ በመሆን ያገለገለችው ሰርካዲስ በኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የተለያዩ የእድሜ እርከኖችም በረዳት አሰልጣኝነት ሰርታለች።

ከሴቶች ቡድን በተጨማሪ ክለቡ ሊያቋቁም ላሰበው የተስፋ ቡድን (ከ20 ዓመት በታች ቡድን) ሁለት አሰልጣኞች ለመጨረሻ ፈተና አልፈው አብርሃም መላኩ ተመርጧል። የቀድሞ የሴንትራል ዩኒቨርስቲ እና አውስኮድ አሰልጣኝ አብርሃም በአሁኑ ሰዓት በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የእግር ኳስ አሰልጣኝነት ትምህርት እየተማረ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪ አሰልጣኙ በከተማው ፍኖተ ጣና የሚባል የታዳጊዎች ፕሮጀክት አቋቁሞ እየሰራ ይገኛል።

ክለቡ ከሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች በተጨማሪ የቴክኒክ ዳይሬክተር ሹመት አከናውኗል። የእግር ኳስ ጁንየር ኢንስትራክተር የሆነው እና በጀርመን ሃገር ከዓለም ከተወጣጡ አሰልጣኞች ጋር ለአምስት ወር የኤ ላይሰንስ (A licence) ስልጠና ወስዶ ያጠናቀቀው መብራቱ ሃብቱ የክለቡ ቴክኒክ ዳይሬክተር ሆኗል።


© ሶከር ኢትዮጵያ