ዝሆኖቹ ለነገው ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት ባህር ዳር ገብተዋል

ነገ በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን የሚገጥሙት ኮትዲቯሮች ከደቂቃዎች በፊት ባህር ዳር ገብተዋል።

41 የልዑካን ቡድን ይዘው ወደ ባህር ዳር የተጓዙት ኮትዲቯሮች በአስገራሚ ሁኔታ ጨዋታው ከሚደረግበት ሰዓት 18 ሰዓታት ብቻ ቀድመው ወደ ባህር ዳር ገብተዋል። ብሄራዊ ቡድኑ 1 ሰዓት አዲስ አበባ ከደረሰ በኋላ በቀጥታ በተያያዥ በረራ ወደ ባህር ዳር ይገባል ተብሎ ቢጠበቅም ባልታወቀ ምክንያት መዘግየቱ ተነግሯል። ቡድኑ ባህር ዳር እንደደረሰም በቀጥታ ወደሚያርፍበት ዊን ሆቴል እንደተጓዘ ታውቋል።

ብሄራዊ ቡድኑ በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም ከጨዋታው 24 ሰዓት በፊት ልምምድ መስራት ሲገባው በጊዜ እጥረት ምክንያት ልምምድ ሳይሰራ የነገውን ጨዋታ ይጠባበቃል። በአሰልጣኝ ኢብራሂም ካማራ የሚመራው ቡድኑ ከዊልፍሬድ ዘሃ በተጨማሪ ፍራንክ ኬሲ፣ ኮናና ጊስላን እና ሳዮባ ማንዴን ሳየይዝ ወደ ባህር ዳር እንዳመራ ታውቋል። ቡድኑ 20 ተጨዋቾችን እና 21 የአሰልጣኝ፣ የህክምና፣ የምግብ እና የፋይናንስ ባለሙያዎችን ይዞ ጨዋታው ወደሚደረግበት ከተማ እንደገባ ተነግሯል።


© ሶከር ኢትዮጵያ